በሐረሪ ክልል ከበጋ መስኖ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው።

5

 

በሐረሪ ክልል የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሮዛ ኡመር በክልሉ በዘንድሮ በጋ የመስኖ ልማት ሥራ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በክልሉ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ከ5 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል።

በክልሉ የመስኖ ልማቱን ለማሳካት የምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሮች መቅረቡንና ለግብርና ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ገበያን የማረጋጋት እና አርሶ አደሮችን ከተረጂነት ማውጣት ዓላማ ማድረጉንም አስረድተዋል።

ለአርሶ አደሩም ሥልጠና መሰጠቱን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ለተግባራዊነቱም የግብዓት አቅርቦት፣ የክህሎት ሥልጠና እና የባለሙያ የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የመስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ በክልሉ በዝናብ እጥረት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በክልሉ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት የሽንኩርት፣ የቲማቲም፣ የጥቅል ጎመን፣ የቃሪያ፣ ካሮትና ሌሎች የአትክልትና የሰብል ዓይነቶች በስፋት የሚለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመስኖ ከሚለማው መሬትም ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ሥራውን ለማሳካትም በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

በቀጣይም በበጋ መስኖ የሚለሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አርሶ አደሩን በቀጥታ ከተጠቃሚው ጋር ማገናኘት የሚያስችል ስራ በላቀ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሳይንሳዊ አሠራሮች ለተሻሉ የግብርና ሥራዎች
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ብርሃን ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።