ሳይንሳዊ አሠራሮች ለተሻሉ የግብርና ሥራዎች

3

 

በአማራ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን እና ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎችን በተግባር እንዲያዩ እና እንዲለማመዱ ከሚደረጉባቸው አሠራሮች ውስጥ አንዱ ነው የአርሶ አደሮች ማሠልጠኛ ማዕከላት እና የሠርቶ ማሳያ ማዕከላት።

በክልሉ የግብርና ኤክስቴንሽንን ለመፍጠር በሺዎች የሚቆጠሩ የአርሶ አደር ማሠልጠኛ እና የሠርቶ ማሳያ ማዕከላት መቋቋማቸውን የሚገልጸው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ እነዚህ ማዕከላት በክልሉ ግብርና ላይ ስር ነቀል ለውጦችን አምጥተዋል ይላል።

በክልሉ በእያንዳንዱ ቀበሌዎች የሚገኙት የአርሶ አደር ማሠልጠኛ ማዕከላት አሁን በክልሉ ላይ ለሚታየው የግብርና የምርታማነት ዕድገት የማይናቅ አበርክቶም አላቸው። እነዚህ ማዕከላት አርሶ አደሮች ከንድፈ ሃሳብ አልፎ በተግባር እንዲማሩባቸው እንደ ሠርቶ ማሳያ መሬት እያገለገሉ ይገኛሉ።

በሠርቶ ማሳያዎች አማካኝነት ለበሽታ፣ ለድርቅ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች (ለምሳሌ የምርጥ ስንዴ፣ በቆሎ እና የጓሮ አትክልቶች ዝርያዎች) አርሶ አደሮች በራሳቸው ማሳ ላይ ከመተግበሩ በፊት በማዕከሎቹ ተሞክረው አፈጻጸማቸው ይታያል። ይህም ቴክኖሎጂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አርሶ አደሮች እንዲገቡ አስችሏል።

እነዚህ ሠርቶ ማሳያዎች የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን፣ የጠብታ መስኖ እና የሞተር ፓምፕ አጠቃቀምን በተግባር በማሳየት አርሶ አደሮች በክረምት ብቻ ሳይኾን በበጋም እንዲያለሙ አቅም ፈጥረዋል። በተለይ በስንዴ መስኖ ልማት ዙሪያ የተከናወኑ ሠርቶ ማሳያዎች አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

ሠርቶ ማሳያዎቹ አርሶ አደሮች ማዳበሪያን በአግባቡ የመጠቀም፣ አፈርን የመመርመር፣ የተሻሻለ የእንስሳት እርባታ እና የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን (እንደ ማጨጃ እና መውቂያ ቴክኖሎጂዎች) አጠቃቀም በቀጥታ በሠርቶ ማሳያ ማዕከላት በመመልከት ወደ የራሳቸው የዕለት ተዕለት የግብርና ልማት እንዲያመጡት ትልቅ መነቃቃትን ፈጥረዋል።

ማዕከሎቹ የልማት ሠራተኞች ከአርሶ አደሩ ጋር የሚገናኙባቸው፣ የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎች የሚሰጡባቸው እና የጋራ ውይይት በማድረግ በባሕላዊ አሠራር ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የግብርና አስተሳሰብ ወደ ሳይንሳዊ እና መረጃን መሠረት ባደረገ አሠራር እንዲቀየርም አግዘዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

በምስጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየቆቦ ጊራና ሸለቆ፤ ከማሾ ልማት እስከ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ምንጭነት
Next articleበሐረሪ ክልል ከበጋ መስኖ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው።