የቆቦ ጊራና ሸለቆ፤ ከማሾ ልማት እስከ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ምንጭነት

4

 

የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ከቆቦ እስከ ጊራና ድረስ 17 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል። እስከ ምንጃር ድረስ የሚዘልቅ ከ73 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን የማልማት አቅምም አለው። አሁን ላይ በአጠቃላይ በሥሩ 42 የመሥኖ ፕሮጄክቶች እየሠሩ ይገኛሉ።

በቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የሆርቲካልቸር ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አንዳርጌ አስማረ እንዳሉት ፕሮግራሙ በማሾ፣ በሌሎች የሰብል አይነቶች እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ላይ በስፋት እየሠራ ይገኛል። ምርጥ ዘሮችን በመጠቀም በዓመት ሦስት ጊዜ እንደሚያመርትም ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ለአሚኮ እንደተናገሩት አካባቢው ቆላማ በመኾኑ በተለይ ለማሾ ምርት የተመቸ ነው። ማሾ በ60 ቀናትም ለምርት ይደርሳል ነው ያሉት። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ዙር የክረምቱ ወቅት ብቻ በ407 ሄክታር ላይ በማምረት 6 ሺህ196 ኩንታል ማሾ ለገበያ ቀርቧል ነው ያሉት። በ965 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ ስንዴ ለማልማት አቅደው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማትም በሥፋት እየተሠራበት መኾኑንም አብራርተዋል። በተለይም ማንጎ እና ፖፖያን በክላስተር አሠራር በመጠቀም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ለክልሉ የምርጥ ዘር ምንጭ እየኾነ መምጣቱንም አብራርተዋል።

ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በ605 ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር እያባዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ለአብነትም በቅርቡ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን የፖፖያ ችግኝን የሚሰጥ 163 ኪሎግራም የፖፖያ ዘር ለክልሉ ማሰራጨት እንደቻለም አንስተዋል።

በ6 ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻለ ምርት የሚሰጥ የሽንኩርት ዘርን በማባዛት እና ወደ አርሶ አደሮች በማሰራጨት ሽንኩርት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት ለመፍታት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እያንዳንዱ የመስኖ ፕሮጄክት በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል እንደሚደረግበት ጠቁመዋል። የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የኬሚካል እና የውኃ አጠቃቀም በየተመደበላቸው ባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ እየተሠራ ስለመኾኑም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌾 የድርቅን ወሰን የሚሻገሩት ዝርያዎች – በምርምር የተበሰረ አዲስ የምግብ ዋስትና ተስፋ!