🌾 የድርቅን ወሰን የሚሻገሩት ዝርያዎች – በምርምር የተበሰረ አዲስ የምግብ ዋስትና ተስፋ!

4

 

ኢትዮጵያ የድርቅ ተጽዕኖን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጎን ለጎን ፈጥነው የሚደርሱ እና ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዓይነቶችን እያስተዋወቀች ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምርታማነትን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ ነው።

ኢንስቲትዩቱ በ2018 ዓ.ም ስድስት የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ማድረሱን የሰብል ምርምር ዳይሬክተሩ ዓለማየሁ አሰፋ (ዶ.ር) አስታውቀዋል። የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የሽንብራ እና የድንች ዝርያዎች ደግሞ ከተለቀቁት መካከል ይጠቀሳሉ።

በምርመር የተዋወቁት እነዚህ ዝርያዎች የዝናብ አጠር አካባቢዎችን ፍላጎት ያማከሉ፣ በመስኖ የሚለሙ፣ ሙቀትን የሚቋቋሙ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ ናቸው።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ያስተዋወቃቸው ሦስቱ አዳዲስ የበቆሎ ዝርያዎች ድርቅን እና አረምን በመቋቋም፣ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ምርት በመስጠት እና እንደ ዋግኽምራ እና በለሳ ላሉ ዝናብ አጠር አካባቢዎች አስተማማኝ መፍትሔ ኾነዋል።

በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀው አዲስ የድንች ዝርያም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚደርስ እና የላቀ ምርታማነትን የሚያስገኝ እንደኾነ ተጠቁሟል።

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም እንደ እንቁ ዳጉሳ እና መልካም ማሽላ ያሉ የብዕር ሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። የማሾ የምርምር ውጤትም ለአርሶ አደሮች ጠንካራ የኢኮኖሚ ምንጭ ኾኗል።

የኤሊኖ ወለድ ድርቅ ስጋትን ለመከላከልም እንደ ሕንድ፣ አውስትራሊያ፣ እስራኤል እና ኬንያ ባሉ ሀገራት የተከናወኑ የድርቅ ተከላካይ ዘሮችን የማባዛት፣ የጠብታ ውኃ ማጠጣት ቴክኖሎጂ እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ማልማት ልምድ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ተግባራት ናቸው።

በኢትዮጵያም ይህንን ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋም ዘመናዊ የውኃ አሥተዳደር እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ማቀናጀት አስፈላጊ በመኾኑ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ሥራውን በማስፋት 14 አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለማስተዋወቅ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#አሚኮ #Climate_Resilience#Drought_Tolerant_Crops​ #Amhara
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article
Next articleየቆቦ ጊራና ሸለቆ፤ ከማሾ ልማት እስከ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ምንጭነት