16

በአማራ ክልል እየታየ ያለው የሰላም ተስፋ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት የክልሉ ሕዝብ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጥልቅ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርጓል።

በዚህም የክልሉ ሕዝብ ከንብረት ውድመት፣ ከእርስ በርስ ግጭት እና ስቃይ እንዲወጣ ብሎም በሰላም ወጥቶ የመግባት እና የልማት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ በየጊዜው ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል።

ዛሬ ግን ክልሉ ሕዝብ የጸጥታ ችግር ተቀርፎ የመረጋጋት ተስፋ እና የሰላም ጎህ እየቀደደ ይገኛል።

የክልሉ መንግሥት የዘረጋውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ እና መደበኛ የኑሮ ማዕቀፍ የሚቀላቀሉ ታጣቂ ኀይሎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

ይህ ከጥፋት መንገድ ወጥተው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው የመመለስ ሐዋርያዊ እርምጃ ለክልላችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሁነኛ እና ታሪካዊ ጅማሮ ነው።

ይህ የሰላም ሂደት በክልሉ ተጨማሪ የሰው ሕይወት እና የንብረት ውድመት እንዳይፈጠር ትልቅ ዋስትና ኾኗል። የክልሉ ሕዝብ በውስጡ ያለውን ቁስል እየታከመ ወደተረጋጋ እና ሰላማዊ የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዲመለስ የማይተካ ተስፋን ጥሏል። እንዲሁም በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እና የፀጥታ መዋቅሩ ሰላምን በብቃት ለማስጠበቅ የሚያስችል ምቹ መደላድልንም ፈጥሯል።

የክልሉ ሕዝብ ከሁሉ በላይ የሚሻው እና የሚናፍቀው ዘላቂ ሰላም ነው፤ የታጣቂዎች መመለስ ለዚህ የተናፈቀ ሰላም ዕውን መኾን ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል። እናቶች ልጆቻቸውን ያለስጋት እና ሰቀቀን በፍቅር እና በሰላም ማሳደግ የሚችሉበት ዕድል በመፍጠር፣ የተቋረጡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በር በመክፈት ሚናው የላቀ ነው።

አርሶ አደሮችም ቢኾን ያለምንም ስጋት ማሳቸውን ማልማት እና ምርታቸውን ወደ ገበያ አውጥተው እንዲሸጡ፣ በግጭት ሳቢያ የተቋረጡ የልማት ሥራዎች ዳግም እንዲቀጥሉ እና የተጎዱ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲያገግሙ ሰላም ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ይህ ሂደት ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

ሰላም ከሁሉም በላይ ቀዳሚው ነገር ነውና አሁንም ትጥቅ አንግበው በጫካ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመጠቀም ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ጥሪ እየቀረቀ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት ያስተላለፉት ጥልቅ መልዕክት ለሰላም ትንሳኤያችን መብራት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “በጫካ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ወደ ሰላማዊ መንገድ ኑ፤ ያኮረፋችሁ ወገኖች የይቅርታን መንፈስ ተላብሳችሁ በሀገር ግንባታ ተሳተፉ፤ የዛሬ ወጣቶች በአርቆ አሳቢነት ነጋችሁን ቅረጹ፤ የትናንት ወጣቶች ካለፈ ስህተታችሁ ተማሩ፤ ከአብዮታዊ የትግል ስልት ራቁ፤ የባንዳነት ልማድን አስወግዱ፤ የተጣሉትን አስተራርቁ፤ የሸሹትንም መልሱ” ነው ያሉት።

“የዛሬ ልጆች በዕውቀት፣ በክህሎት እና በሥነምግባር ታንጻችሁ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመውረስ ተሰናዱ፤ የሀገር አባቶች እና እናቶች ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅነት እና ሥልጣኔ ጸልዩ፣ ታሪካችሁን አውርሱ፤ ትውልዱንም ገንቡ።” ብለዋል።

ይህ የሰላም አማራጭ አካሄድ በክልላችን የዘላቂ ሰላም እና የዕድገት ምዕራፍን ለማብሰር ትልቅ የማዕዘን ድንጋይ ኾኖ ብሩህ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#አሚኮ #Energy_Transition
#CostOfLiving_Relief #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_20_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ብርሃን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልገሎት መርቀው ሥራ አስጀመሩ።
Next article🌾 የድርቅን ወሰን የሚሻገሩት ዝርያዎች – በምርምር የተበሰረ አዲስ የምግብ ዋስትና ተስፋ!