
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ በተሁለደሬ ወረዳ በ4 ቀበሌ በሺዲፕ ፕሮጀክት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ የአዋሽ ወንዝ የመስኖ ግንባታን አስመርቋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች አሊ ይማም እና ይማም ሠይድ ከዚህ ቀደም በባሕላዊ መንገድ ይጠቀሙት የነበረውን የመስኖ ሥራ በዘመናዊ መልኩ መተግበሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
በዓመት ሦሥት ጊዜ በማልማት ውጤታማ ለመኾን ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።
የሺዲፕ ፕሮጀክት የአማራ ክልል አስተባባሪ ሙጨ ደመቀ ፕሮጀክቱ በተሁለደሬ ወረዳ ለነበረው የሥራ ቆይታ የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ እና ክትትል አስደሳች እንደነበር ገልጸዋል። በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅም ድጋፉ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት ካናል መሠራቱን ተናግረዋል።
ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተሠራው የመስኖ ግንባታ ከ146 በላይ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ከ85 ሄክታር መሬት በላይ እንደሚያለማም አመላክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን የዞኑ አርሶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። በዚህም የፍራፍሬ ልማት ላይ አመርቂ ውጤት መምጣቱን ነው የተናገሩት። የባለሙያን ምክረ ሀሳብ በመተግበር የምርት ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
መሰል ፕሮጀክቶችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፋት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ እታገኝ አዳመ አርሶአደሮች በአካባቢ የሚገኝን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የምርት ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#አሚኮ #መስኖ_ልማት #ግብርና #አማራ_ክልል
#ደሴ #ጥቅምት_21_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ሕይወት አስማማው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
