“ሕዝብ ያመነበት የሰላም እና የልማት ሥራ መሠረቱ የጸና ነው” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር

5
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ከአገው ግምጃ ቤት ከተማ አሥተዳደር እና ከአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም በመኾኑ ለአካባቢያቸው ዘልቂ ሰላም መስፍን ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ተጀምረው የቆሙ የአስፋልት መንገዶች ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ የአመራር ቁርጠኝነት እንዲረጋገጥ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመብራት ኀይል አቅርቦት እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን የሚገቱ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በተለያዩ ሕዝባዊ ወይይቶች የተነሱ የሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ከተስፋ ወደ ተግባር መቀየር አለባቸውም ነው ያሉት።
የአገው ግምጃ ቤት ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃየሁ አስረስ የኅብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ለመመለስ የከተማዋን የገቢ አቅም ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
እያደገ የመጣው የልማት ፍላጎት በውስን የመንግሥት በጀት ብቻ የሚመለስ አለመኾኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለማረጋጋት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ባሻገር ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በወሰደው ቁርጠኝነት በማኅበር ተደራጅተው የቤት መስሪያ ቦታ ሲጠባበቁ ለቆዩ 1ሺህ 500 ዜጎች መሬት የማስተላለፍ ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አየን ብርሃን መንግሥት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መጠነ ሰፊ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተጀምረው የቆሙ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና አሥተዳዳሪው ተጀምረው የተጓተቱ እና ግንባታቸው የቆሙ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንት ማነቆ የኾነው የመብራት መቆራረጥ እና የኀይል አቅርቦት ማነስ ምላሽ እንዲያገኝ ከሚመለከተው የመንግሥት መዋቅር ጋር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ሕዝብ ያመነበት የሰላም እና የልማት ሥራ መሠረቱ የጸና ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነፃነት የሚነፍጉ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በጋራ መታገል ይገባልም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሙስና እና ብልሹ አሠራርን ቀድሞ የመከላከል ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
Next article“መንግሥት ማቀድ ብቻ ሳይኾን ማጠናቀቅ እና ቃል የገባውን መፈጸም መለያው አድርጎ እየሠራ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)