
የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት ሥራ ወደ ተግባራዊ ተጠቃሚነት እየተሸጋገረ ይገኛል። የጋዝ ሀብቱንም ለታክሲ ትራንስፖርት፣ ለፋብሪካዎች ግብዓት እና ለኑሮ ውድነት ማቃለያነት ለማዋል ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አስታውቀዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በጎዴ ከተጀመረው የጋዝ ምርት በኋላ ሀብቱን ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ ውሥብሥብ እና ቴክኒካዊ ሂደቶች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
ጋዙን ከጉድጓድ አውጥቶ ለማጓጓዝ እና ለመጠቀም ልዩ ማደያዎች፣ ልዩ ታንከሮች እና የባስ ሞተሮችን ወደ ጋዝ ተጠቃሚነት የሚቀይር አሠራር መዘርጋቱንም አስረድተዋል። እስካሁንም 26 የሚጠጉ የአንበሳ ባሶች ሞተር ተቀይሮ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።
ሂደቱን ለማፋጠን 400 አዳዲስ የጋዝ ባሶች እና ወደ 100 የሚጠጉ የጋዝ ትራኮች መታዘዛቸውን እና ጎን ለጎንም ነባር የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ወደ ጋዝ ተጠቃሚነት የመቀየር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሽግግሩ የትራንስፖርት ወጪን በ50 በመቶ እንደሚቀንሰው እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫና እንደሚያቃልለው አረጋግጠዋል። ምግብ፣ መኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት ወጪዎችን መቀነስ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ቁልፍ መኾናቸውንም አመላክተዋል።
መንግሥት ማቀድ ብቻ ሳይኾን ማጠናቀቅ እና ቃል የገባውን መፈጸም መለያው አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል። ጋዝን ለኀይል፣ ለማዳበሪያ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የማዋል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ልማት እና ሰላም ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያመጣ መኾኑንም ጠቁመዋል። ዜጎች በጋራ በመትጋት እና ተስፋን ሰንቀው ሀገርን በመገንባት ሂደት አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_20_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
