
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ያላት የመሪነት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ይች የምሥራቅ አፍሪካ ታላቅ ሀገር አሁን ላይ ያላትን ተጽዕኖ ማየት የጀመሩ ሀገራት እየተበራከቱ ነው።
ከእነዚህ ሀገራት መካከል ሩስያ ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች። ኢትዮጵያ ማንነቷን እና አቅሟን በዓለም አቀፍ ደረጃ መግለጽ በመጀመሯ ሩስያ ከዚች ሀገር ጋር ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎትን አሳይታለች።
በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ምስክር ከተማ እንደሚሉት ሀገራት በዓለማቀፍ ደረጃ ተጽዕኗቸውን የሚጨምረው በሚሠሩት ዲፕሎማሲ እንደኾነ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ አፍሪካ ከቀሪው ዓለም የነበረባት የመረሳት ሁኔታ ተሻሽሎ በርካታ ጠንካራ ሀገራት ወደዚች አሕጉር እያማተሩ ስለመኾኑ ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩ ነው የጠቆሙት።
ከእነዚህ ሀገራት መካከል ደግሞ በጂኦ ፖለቲካ አቀማመጧ የተሻለችው ኢትዮጵያ እንደኾነች እና አሁን ላይ ሀገሪቱ ያላትን አቅም ተገንዝባ ባላት ተጽዕኖ ልክ የሚገባትን ለማግኘት እየሠራች ነው ብለዋል።
ለዚህም ማሳያው በሩስያ የአፍሪካ ጉባኤ ላይ የነበራት ተቀባይነት ከሌሎች ሀገራት በተለየ ከፍ ብሎ መታየቱ እና ከፍ ያሉ ስምምነቶች መፈጸማቸው ሀገሪቱ አፍሪካን በመወከል ተጽዕኖ ልትፈጥር እንደምትችል በመገንዘባቸው እንደኾነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ብዙ የመልማት አቅም እንዳላት የተገነዘቡት ሩስያውያን ከሀገሪቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ወስነዋል ነው ያሉት።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮብ ሀገሪቱ ወደ ቀይ ባሕር እንድትመለስ ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት የገለጹትም ኢትዮጵያን በቀጣናው አጋር ማድረግ እና አጋፋሪ እንድትኾን ማስቻል በአካባቢው ያለውን ደኅንነት እንደሚያረጋግጥ እና ጥቅማቸውን እንደሚያስጠብቅላቸው በማመናቸው እንደኾነም ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ አሁን ያሳካችውን የመንግሥት ለመንግሥት ዲፕሎማሲን በሌሎች ዘርፎችም ማሳደግ ይገባታል ነው ያሉት።
በርካታ ሀገራት በመላው ዓለም በሚገኙ ዜጎቻቸው ዲፕሎማሲን እንደሚሠሩ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚም እንደኾኑት ሁሉ ኢትዮጵያም በመላው ዓለም በርካታ ዜጎቿ ያሉ በመኾኑ እነዚህን ዜጎቿን የዲፕሎማሲው አጋር ማድረግ እንደሚገባትም ነው የጠቆሙት።
ከመንግሥት ለመንግሥት በተጨማሪ የዜጋ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱን ከፍ የሚያደርግ እና ያላትን የባሕር በር ጥያቄም ኾነ ሌሎች ፍላጎቶቿን ለቀሪው ዓለም ለማስገንዘብ ትልቅ ኀይል በመኾኑ በስፋት መጠቀም ይገባታል ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_20_2019_ዓ_ም
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
