🚜🌾 የሰብል ብክነትን የሚያስቀረው የሜካናይዜሽን ጉዞ 🇪🇹

4

አየለ ለማ በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረት እና ጅሩ ወረዳ በግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም የካበተ ልምድ ያላቸው አርሶ አደር ናቸው። ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባለፈ ለሌሎች አርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ።

የግብርና ቴክኖሎጂን ምርት ለመሠብሠብ መጠቀም ጊዜን እና ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ጥራትን በመጠበቅ ያለ አግባብ የሚወጣ ወጪን ያስቀራል ይላሉ። ሌሎችም አርሶ አደሮች ይህንን አሠራር በመተግበር ተጠቃሚ እንዲኾኑ መክረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ችሮታው አስፋው በዘንድሮው የምርት ዘመን ዘመናዊ የግብርና አሠራርን በመከተል የሰብል ብክነትን ለመቀነስ እና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ሰፊ የሰብል ሥብሠባ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

በዞኑ 30 ሺህ ሄክታር መሬት በኮምባይነር እና 70 ሺህ ሄክታር መሬት በትሬሸር ለመሠብሠብ እና ለመውቃት ታቅዷል ነው ያሉት።

​በዞኑ የቴክኖሎጂ ልምድ ባላቸው እንደ ሞረትና ጅሩ፣ ሲያደብርና ዋዩ እና በሌሎችም አካባቢዎች በስፋት የሚተገበር ነው። በዘንድሮው ዓመት ግን ሰፋፊ የስንዴ ኩታገጠም በተዘሩባቸው እና ልምዱ ባልነበራቸው ወረዳዎች ጭምር በኮምባይነር የመሠብሠብ ባሕል እንዲጀምሩ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

​የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የመኸር ሰብሎችን በቴክኖሎጂ በመሠብሠብ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ 40 በመቶ የሚኾነውን የእርሻ ሽፋን በቴክኖሎጂ የመሠብሠብ ልምድ መኖሩን ነው የገለጹት።

ቴክኖሎጂ አርሶ አደሮችን ከከባድ የጉልበት ሥራ ነጻ በማውጣት ድካምን ይቀንሳል ብለዋል። ሰብሉን በማጨድ፣ በመውቃት እና በማጓጓዝ ሂደት ሊባክን የሚችለውን ሰብል እስከ 30 በመቶ በመቀነስ የምርት ብክነትን ያስቀራል ነው ያሉት።

በባሕላዊ አውድማ ከሚከሰት አፈር እና ቆሻሻ የጸዳ፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲገኝ ያደርጋል ብለዋል። ሰብሉን በፍጥነት ሠብሥቦ መሬቱን ለቀጣይ የመስኖ ሥራ በፍጥነት ለማዘጋጀት ጊዜን እንደሚቆጥብም አንስተዋል።

አርሶ አደሮችን ከቴክኖሎጂው ጋር በማላመድ እና እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል ያሉት ምክትል ኀላፊው በክራይ ጭምር በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሠብሠብ አንደሚገባ አመላክተዋል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_20_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ – የኢትዮጵያ አዲሱ ጉልበት 🇪🇹