ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ቀድሞ የመከላከል ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

4
በአማራ ክልል የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን መከላከል ጥምረት የ2018 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ ክልላዊ መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ የሥነ ምግባር ግንባታ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ጥምረት መመሥረቱን አውስተዋል።
ጥምረቱ እንደተቋማቱ ባህሪ ሥነ ምግባርን የመገንባት፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ቀድመው እንዲከላከሉ የማስቻል፣ ተፈጽሞ ሲገኝ ተጠያቂ እንዲያደርጉ እና አሠራርን ዲጅታላይዝ በማድረግ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን እንዲከላከሉ የማድረግ ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።
ሙስና እና ብልሹ አሠራርን የመከላከል ሥራ በኮሚሽኑ ብቻ የሚሠራ ሳይኾን ሁሉም ተቋማት በጋራ የሚሠሩት ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ከአሁን በፊት ምክር ቤቱ ሲያደርገው የነበረውን ክትትል የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል ሁሉም ባለቤት ኾኖ እንዲሠራ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ጥምረት መመሥረት ያስፈለገው የሥነ ምግባር ግንባታን፣ ብልሹ አሠራርን የመከላከል ሥራን ሁሉም ተቋም በባለቤትነት እንዲመራ ለማስቻል መኾኑን ገልጸዋል።
ጥምረቱ በምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ባለፉት ዓመታት ብልሹ አሠራርን በመከላከል እና ስለ ብልሹ አሠራር በማስተማር፤ ተፈጽሞ ሲገኝ በማረም፣ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።
ሙስና በባህሪው የመንግሥት አገልግሎት እንዲዛባ፤ የመንግሥት ሃብት በግለሰቦች እንዲገባ፤ የተቋማት አገልግሎት አሠጣጥ እንዲዳከም የሚያደርግ እና የግጭት መንስኤ የሚኾን ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ሙስና እና ብልሹ አሠራር በምክክር ኮሚሽን ከተያዙ አጀንዳዎች ውስጥ መኾኑን አስታውሰዋል። በሀገር እና በሕዝብ ላይ አስከፊ ጉዳት የሚያመጣ በመኾኑ የማስተማር እና ቀድሞ የመከላከል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ተቋማት በሥነ ምግባር ግንባታ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በመከላከል፣ ተጠያቂነትን በማስፈን እና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ያከናወኗቸው ተግባራት አፈጻጸም በጥምረቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰማዩ ዐምድ_ የሉዓላዊነት መተማመኛ።
Next article“ሕዝብ ያመነበት የሰላም እና የልማት ሥራ መሠረቱ የጸና ነው” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር