
አሁን ወቅቱ የዓለም ኀያላን ሀገራት የኀይል ሚዛን አሰላለፍ ውሥብሥብ ደረጃ የደረሰበት ነው። ከምዕራቡ እስከ ምሥራቁ የዓለም ዳርቻ የሚስተዋለው የኀያልነት ፍጥጫ እና የጎራ አሰላለፎች የዓለምን ተፈጥሯዊ ቅርጽ የሚቀይሩት ይመስላል።
በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣናም ቢኾን የጂኦፖለቲካ ውጥረት ያየለበት፣ የፍጥጫ ማዕበሉ የገነፈለበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ታዲያ በዚህ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና ጅኦፖለቲካዊ ፉክክሩ ባየለበት ወቅት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እና ብሔራዊ ጥቅሟን በሰላም እና በጽናት ማዕቀፍ ውስጥ ለማቆም በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በወታደራዊ ጽኑ ዝግጅት፣ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም እና በሠለጠነ የሠራዊት ክንድ የተገነባች የጽናት ግንብ ኾናለች። በውስጥ እና በውጭ ኀይላት የሚሰነዘሩባትን ማናቸውንም የደኅንነት ስጋቶች አስቀድሞ በመግታት ረገድ የደረሰችበት ደረጃ ብሔራዊ ደኅንነቷን ወደ ላቀ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ የኀይል አሰላለፍ ፍጥጫ ባየለበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ የገነባችው ጠንካራ የመከላከያ አቅም ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን አስገኝቷል።
በተለይም የአየር ክልሏን በማይበገር የብረት አጥር በማዋቀሯ እና የቀጣናውን የኀይል ሚዛን በባለቤትነት በመቆጣጠሯ የቀጣናውን የጸጥታ መዋቅር በባለቤትነት እንድትመራ አስችሏታል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀው የኢትዮጵያ አየር ኀይል እና የመከላከል አቅም የሀገሪቱን ሰማይ ከማናቸውም የውጭ ስጋት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉ ሉዓላዊነቷን ከብረት የጸና አድርጎታል። የመከላከያ ሠራዊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ እያደገ መምጣት ደግሞ ከማናቸውም የውስጥ እና የውጭ ጠላት ሴራዎች እና የደኅንነት ስጋቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድመው እንዲከሽፉ የማድረግ የማይናወጥ አቅም ተጎናጽፏል።
ለዚህ ማሳያ የሚኾነው አየር ኀይሉ ከዚህ ቀደም ከታጠቃቸው ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች በተጨማሪ የሱ-35 (Su-35) 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶችን መታጠቁ ነው።
ኢትዮጵያ ከሩሲያ የተረከበቻቸው የሱ-35 አውሮፕላኖች በዓለም ላይ ካሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ግንባር ቀደም መሣሪያዎች ናቸው። ከአየር ወደ አየር፣ ከአየር ወደ ምድር ውጊያ የማካሄድ ከፍተኛ አቅም ያላቸው እና በተግባር የተፈተኑ መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አረጋግጠዋል።
ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ለሀገር ሕልውና ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የነበሩት የሱ-30 እና የአሁኖቹ የሱ-35 ተዋጊ ጄቶች የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ጸንቶ መቆም እና የቴክኖሎጂ የላቀ አቅም መጎናጸፍ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የመላው አፍሪካውያን ኩራት እና የድል አክሊልም ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
