“አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራት እንሞግታለን” የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

2
ሦሥተኛው የሩሲያ –አፍሪካ ጉባኤ በሞስኮ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉባኤው አፍሪካ እና ሩሲያ ግንኙነታቸውን የበለጠ ያጠናከሩበት መኾኑን ገልጸዋል።
ሩሲያ እና አፍሪካ በጠንካራ የወዳጅነት እና የቅርብ አጋርነት የተሳሰሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ባለብዙ ዋልታ እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የኾነ የዓለም ሥርዓትን በመገንባት ሂደት ውስጥ አጋሮች ነን ብለዋል። ግንኙነታቸው በመከባበር ላይ የተመሠረተ መኾኑንም አንስተዋል።
የቀድሞውን የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ ንግግርን ጠቅሰው “ነጻነት ማለት በራስ ጥንካሬ ላይ መደገፍ ማለት ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የምትቆመው የአሕጉሪቱ ሀገራት ለነጻነት፣ ለእውነተኛ ነጻ ልማት እና የራሳቸውን የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ለመምረጥ የሚያደርጉትን ጥረት በሙሉ ጥንካሬዋ እየደገፈች ነው ብለዋል።
ሩሲያ የአፍሪካ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ሲያስጠብቁ፣ ሲያድጉ፣ ኢኮኖሚያቸውን እና ማኅበራዊ ዘርፎቻቸውን ሲያጠናክሩ ለማየት ፍላጎት የነበራት እና አሁንም ፍላጎት ያላት መኾኗን ማጉላት እፈልጋለሁ ነው ያሉት። እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱንም አንስተዋል። ብዙ የሩሲያ ኩባንያዎች በአፍሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በስኬት ሲተገብሩ መቆየታቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በኃይል ማመንጨት፣ የኑክሌር ኃይል ለሰላማዊ ጥቅም ማዋል፣ የማዕድን ማውጣት፣ የኢንዱስትሪ ትብብር፣ ሎጀስቲክስ፣ ቱሪዝም እና ሌሎችንም በርካታ ዘርፎች ላይ እየሠሩ ናቸው ብለዋል።
የሩሲያ ተቋማት ከአፍሪካ አጋሮቻቸው ጋር ባላቸው ትብብር ሁልጊዜ ታማኝነትን፣ አክብሮትን እና በጎ ፈቃድን ያሳያሉ ነው ያሉት። ከአጋሮቻቸው ጋር በዕኩልነት ይሠራሉ፤ የቀደሙት የቅኝ ግዛት ኃይሎች ያደርጉት እንደነበረው ትርፍን ጭልጥ አድርገው ከመውሰድ ይልቅ ያገኙትን ገቢ መልሰው ለልማት ያውላሉ ነው ያሉት።
የላቁ ቴክኖሎጂዎችን እና ልምዶችን ያካፍላሉ፣ የሀገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮችን በሰፊው ይጠቀማሉ፣ አዳዲስ የማምረቻ ተቋማትን ይገነባሉ፣ የሥራ ዕድሎችንም ይፈጥራሉ ብለዋል።
በአፍሪካ ውስጥ የሚሠሩ የሩሲያ ኩባንያዎች አስፈላጊ በኾኑ ሰብዓዊ ጥረቶች ላይ እንደሚሳተፉ እና የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ሂደቶችን እንደሚያከብሩም ገልጸዋል።
ሩሲያ ለአፍሪካ ገበያዎች አስተማማኝ የምግብ እና የግብርና ምርቶች አቅርቦት ሰጪ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህም በአሕጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተጨባጭ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
አፍሪካ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና የግብርና ምርትን በአግባቡ በማደራጀት ወደፊት እራሷን መመገብ ብቻ ሳይኾን የበርካታ የምግብ ምርቶች ዋና ላኪ መኾን እንደምትችል እናምናለን ነው ያሉት። ሩሲያ የግብርና ልምዷን እና ቴክኖሎጂዎቿን ለአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ዝግጁ መኾኗን ተናግረዋል።
ሩሲያ በጤናው ዘርፍ ለአፍሪካ ድጋፍ እያደረገች መኾኗንም ገልጸዋል። የሩሲያ እና የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ፖለቲካ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም በብዙ መልኩ የተቀራረበ እና ተመሳሳይ መኾኑን አንስተዋል።
ሩሳያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ሚና ለማሳደግ በሁሉም መንገድ ትጥራለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት ሥርዓት፣ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው እንሞግታለን ነው ያሉት።
ሩሲያ እንደተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነቷ በአፍሪካ አሕጉር ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እና አዳዲስ ግጭቶችን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ታደርጋለች ብለዋል። ይህንን ስታደርግ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” የሚለውን መርሕ ታከብራለች ነው ያሉት።
ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በወታደራዊ ትብብሮች ላይ በጋራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሩሲያ እና የአፍሪካ ግንኙነት ወደፊት ትልቅ ተስፋ ያለው መኾኑንም አመላክተዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በባሕር ዳር መሬት ወስደው ወደ ሥራ የማይገቡትን ነጥቆ ለሚያለሙት ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው” አቶ ጎሹ እንዳላማው
Next articleባሕር ዳር ዓባይን እና ጣናን በአግባቡ በመጠቀም የአትክልት እና ፍራፍሬ ምንጭ ልትኾን ይገባል።