
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ በከተማዋ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ላይ አደጋ፣ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አፈጻጸም ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኢኮኖሚውን በኢንዱስትሪ መምራት ለአንድ ሀገር ልማት እና ብልጽግና ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥትም ለዘርፉ ልዩ የፖሊሲ፣ የሕግ እና የአሠራር ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ባሕር ዳር ከቱሪዝም ባሻገር ከ300 በላይ ሥራ ላይ ያሉ፣ ከ700 በላይ መሬት የወሰዱ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙባት የኢንዱስትሪ ማዕከል እየኾነች መምጣቷን ጠቁመዋል።
መሬት ወስደው ሳያለሙ የሚያጓትቱትን አካላት ወደ ሥራ ለማስገባት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው፤ ወደ ሥራ የማይገቡትን ነጥቆ ለሚያለሙት ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማ እንዲኾን አስተማማኝ የውስጥ እና የውጭ ሰላም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎች ዋና አንቀሳቃሽ ኀይል ሰው በመኾኑ የሠራተኞችን ጤና፣ ደኅንነት እና መብት ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል። አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች ጥንቃቄ የጎደለው የሥራ ስምሪት እንደሚከተሉም ገልጸዋል።
ለሠራተኞች ተገቢውን የደኅንነት ልብስ እና መሣሪያ በማሟላት ጤናማ እና ሰላማዊ የሥራ አካባቢ በመፍጠር ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምክክሩ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ከሠራተኛ ተወካዮች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር የተደረገ ነው።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
