
ወጣት እንኳየሁ ተሻገር ትባላለች። በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሙያ ሥልጠና እየወሰደች አግኝተናታል።
ቀደም ሲል በቂ ሥልጠና ሳይኖራት በሕገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ ውጭ ሀገር ባደረገችው ጉዞ ምክንያት የደረሰባትን እንግልት እና ፈተና ታስታውሳለች።
“ያለ ሥልጠና በደላላ ወደውጭ ሀገር መሄድ ለበደል እና ለከፍተኛ ችግር ይዳርጋል” ስትልም አጫውታናለች። በተለይም በቋንቋ አለመግባባት እና ሥራን በአግባቡ ባለ ማወቅ ምክንያት በስደት ሀገር ለሦስት ወራት ያህል በችግር እና በእንግልት ውስጥ ማለፏን ነው የገለጸችልን።
አሁን ላይ ያንን መራራ ታሪክ በሥልጠና ለመቀየር የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና እየወሰደች እንደኾነ ነው የነገረችን። በተለይም አስፈላጊ የሙያ ብቃት ሠልጥኖ መሄድ በሥራ ቦታ የሚያጋጥምን ጫና በእጅጉ እንደሚቀንስ ከልምድ ተሞክሮ አጋርታለች።
አዲስ ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ የመሰማራት ዕቅድ ያላቸው ወገኖች ሁሉ ይህንን ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲከተሉ እህታዊ ምክሯን ለግሳለች።
በኮሌጁ የሆቴል እና ቱሪዝም የትምህርት መስክ አሠልጣኝ የኾኑት አስታጠቅ ሰይድ ለሠልጣኞች ለውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት የሚያግዙ የቤት አያያዝ፣ የምግብ አዘገጃጀት እና ሌሎችንም የሙያ ዓይነቶች በንድፈ-ሃሳብ እና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሙያ ማረጋገጫ ወረቀት ያለው የሰው ኃይል በዘርፉ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለው የገለጹት አሠልጣኟ፤ ሠልጣኞች በአሠሪዎቻቸው ዘንድ መብታቸውን ማስከበር የሚያስችላቸውን መልካም ዕድል የሚፈጥርላቸው መኾኑንም ነው ያስረዱት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ የሥራ ስምሪት እና ኢንዱስትሪ ግንኙነት ቡድን መሪ ዘውዱ ደሳለኝ ቀደም ሲል የነበረው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚከናወንበት፤ ቁጥጥር እና በቂ ሥልጠና የማይታይበት፤ የዜጎችን ደኅንነት እና መብት ለአደጋ የጣለ ሰፊ ክፍተት የነበረበት መኾኑን አውስተዋል። ይህንን አካሄድ ሥርዓት ለማስያዝ አዋጅ ወጥቶ ሢሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
በቅርቡ የወጣው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1389/2016 የዜጎችን ደኅንነት፣ መብት እና ጥቅም ሙሉ በሙሉ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ጠንካራ ድንጋጌዎችን አካትቷል ብለዋል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በመመሪያው መሠረት የተጠያቂነት ሥርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት።
ሥራ ፈላጊዎችን በሙያ ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት ብቁ የማድረግ እና የሠለጠነ የሰው ኃይል የማሰማራት ተግባራት እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።
በዚህም በ2018 ዓ.ም በርካታ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። ሠራተኞች ውላቸውን ሲጨርሱም በሰላም ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት አሠራር ተዘርግቷልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
