
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ባሕር ዳር በሁለገብ የኢኮኖሚ ዕድገት መጓዝ የምትችል ከተማ መኾኗን ተናግረዋል። የከተማዋ መሬት ለግብርና ልማት የሚኾን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው መሬቷ ሁልጊዜም ለላቀ ልማት የሚውል መኾን አለበት ብለዋል።
ባሕር ዳር ዓባይን እና ጣናን በአግባቡ በመጠቀም የአትክልት እና ፍራፍሬ ምንጭ መኾን እንደሚገባትም አንስተዋል። ለዚህም አርሶ አደሮች ከተበጣጠሰ የማምረት ሥርዓት ወጥተው በኩታገም ማምረት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በበጀት ዓመቱ መጭውን ዘመን የገበያ ሁኔታ፣ ሙያን እና አቅምን መሠረት ያደረገ ውጤታማ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሰውዘር ደመላሽ ከተማዋ ሰፊ የመሬት፣ የውኃ ሀብት እና ለግብርና ተስማሚ የኾነ ሥነ ምሕዳር አላት ብለዋል።
ይህንን ምቹ ሥነ ምሕዳር በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በበጋ መስኖ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የበጋ መሥኖ ልማት የአርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የመሪዎች ቁርጠኝነት እና የተቋማት ቅንጅትን የሚጠይቅ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
