
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት 129 ዓመታትን የዘለቀ ነው። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በ1890 ዓ.ም በይፋ ይጀመር እንጂ ከዚያ በፊት ወዳጅነት ነበራቸው።
በተለይም በደርግ አሥተዳደር እና በሶቪየት ኅብረት መካከል የነበረው ወታደራዊ እና ሎጂስቲካዊ ትብብር ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጎታል።
ታሪካዊው አጋርነት በዚህ ዘመንም በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተጠናክሮ ቀጥሏል። ፕሬዝዳንት ፑቲን እንዳሉት የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጡ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሻቀቡ የኢኮኖሚ ትብብሩ እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
ሀገራቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በብሪክስ መድረኮች የጋራ አቋም በመያዝ ሉዓላዊነትን የሚያከብር እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይከተላሉ።
በወታደራዊ እና ጸጥታው መስክ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደ ሱ-35 የጦር ጄቶች እና ኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ጨምሮ የሩሲያ ስሪት መሣሪያዎችን በመጠቀም እና የቴክኒክ ሥልጠናዎችን በማግኘት ረገድ የቆየ ትብብርም አላቸው።
በተግባር እየተገለጠ ያለው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ኢትዮጵያ የኤስ-400 ሲስተም ስትረከብ እና የሱ-35 ጄቶችን በሙሉ አቅም መጠቀም ስትጀምር ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን በማክሸፍ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆየት ያግዛል።
በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍም ሩሲያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት እየደገፈች እንደምትገኝ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አረጋግጠዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በተጀመረው የኒውክሌር ትብብር ሩስያ በዘርፉ ያላትን ሰፊ አቅም እና ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መኾኗንም አረጋግጠዋል። የኒውክሌር ፕሮጀክቱ ለኀይል ማመንጫ እና ድህነትን ለመቀነስ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው።
ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ መማራቸው ለሁለቱ ሕዝቦች ሰብዓዊ መሠረት እንደጣለም የሀገራቱ መሪዎች አረጋግጠዋል። የሩሲያ መሪዎች የኢትዮጵያን ሃሳብ እና እምነት በራሳቸው ቋንቋ መረዳት መቻላቸው ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገውም ታምኖበታል።
እ.ኤ.አ. በ2023 በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት መጀመሩ የሁለቱ ሀገራትን የባሕል እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ያሳያል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት፣ የኤክስፖርት መጠንን የማሳደግ ፍላጎት እና ሩሲያ ለአፍሪካ ሀገራት የምታደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ግንኙነቱን ይበልጥ ያሳድገዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
