
በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙት መርሐ ግብሮች መካከል የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት አንዱ ነው። በዚህም የክልሉ መንግሥት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ይገኛል።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የኾነው የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው የካቲት 2016 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይም በጀት ተይዞለታል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ እንደተናገሩት የትምህርት ቤቱ የግንባታው አፈጻጸም ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል። በቅርቡ ወደ መማር ማስተማር ሥራው ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም ትምህርት ቢሮው የሰው ኀይል ማሟላት፣ የመምህራን ቅጥር እና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተው የሚማሩ ተማሪዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በቅርቡ ለተማሪዎች ጥሪ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ሦሥቱም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ሲገቡ በክልሉ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር እንዲሚያሳድጉም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
