
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘመኑን በዋጀ አግባብ ለዜጎች ሕልውና፣ ለሀገር ደኅንነት፣ ለሉዓላዊነት እና ለስትራቴጂካዊ የሃብት ግንባታ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የልማት እና የጥንካሬ ዲፕሎማሲ መልክ ይዞ ይገኛል።
የውጭ ግንኙነት ስኬት ሁልጊዜም በድርድር ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን በመሪዎች መካከል ባለ ቀጥተኛ ግንኙነት የሚፈቱ ወሳኝ መሠረቶችም ያሉት ነው። ኢትዮጵያ ከባሕላዊ የውጭ ግንኙነቷ ባለፈ ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ባለቤቶች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲኾን አድርጋለች።
የዚህ ማሳያው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት ቀጥተኛ ውይይት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ርክክብን አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸው ነው።
ይህም የከፍተኛ መሪዎች ዲፕሎማሲ የሀገርን ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ጊዜ ሳይገድበው በፍጥነት ለማሳካት ያለውን አቅም በግልጽ ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ባላት ንቁ እና የላቀ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የሀገርን የመከላከል አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳደግ የሚያስችል ነው። ይህ የዲፕሎማሲ እርምጃም ሀገሪቱ የአየር ክልሏን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው
በዘመናዊው ዓለም የሉዓላዊነት ጽንሰ-ሐሳብ ከፖለቲካዊ ነጻነት ባለፈ በወታደራዊ እና በቴክኖሎጅ ራስን የመቻል አቅምን ማሳደግ ይጠይቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት ብዙ ሀገራት ችግር ከመፈጠሩ በፊት በሰላም ጊዜ በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣሉ።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እና የደኅንነት ስትራቴጂ ግን “ሰላምን ፈልግ የሚለውን ጥልቅ መርሕ መከተል ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ራሷን ከማንኛውም የውስጥ እና የውጭ አደጋ በቅድመ-ዝግጅት ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለች ትገኛለች።
የዲፕሎማሲው ዋና ግብ የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የነገዋን ሀገር ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ነው። ዛሬ የሚከናወኑ የመከላከያ አቅም ግንባታዎች ነገ ሀገርን በኩራት እና በሰላም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የጽኑ ዋስትና ማዕዘናት ናቸው።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቿ የምታስመዘግባቸው እነዚህ ድሎች የሉዓላዊነቷን ማጠናከሪያ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ክብደት እና ተሰሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
