
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እየደረጀ እና እየጠነከረ መጥቷል። በመተማመን፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በታሪክ፣ በባሕል፣ በሃይማኖት እና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው ሁለቱ ሀገራት አሁን ደግሞ በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂ ያላቸው ትብብር የላቀ ኾኗል። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች ግንኙነታቸውን የበለጠ እያጠናከረው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ውይይታቸው በኒውክሊየር ኀይል፣ በጤና እና ንግድ ዘርፎች ያለውን ትብብር፣ በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮችን ያካተተ እንደነበር አንስተዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ወዳጃዊ እና ሁልጊዜም ፍሬያማ የኾነው ግንኙነታችንን በእጅጉ አደንቃለሁ ማለታቸውን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በሁለቱ ሀገራት መከካል ሰፊ የጋራ ትብብር እና ፕሮጄክቶች እንዳሉም ገልጸዋል።
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ይቆማሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በባለብዙ ወገን መድረኮች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በብሪክስ ውስጥ ውይይት እናደርጋለንም ብለዋል።
ሩሲያ አፍሪካ የአዲሱ የብዙ ዋልታ ዓለም ሥርዓት ቁልፍ ማዕከል ኾና ብቅ ማለቷን ሙሉ በሙሉ ትደግፋለች ነው ያሉት። ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የንግድ እና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋት፣ የምግብ እና የኀይል ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የጤና ጥበቃን ለማልማት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
በሩሲያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ሁለገብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ብዙ ዕድሎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
በጽናት የሚታወቁት ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ጥብቅ ግንኙነት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሚዛንን ለመጠበቅ፣ የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስቀደመ፣ በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሠረተው ዲፕሎማሲዋ ውጤት እያመጣላት ነው።
ኢትዮጵያ ወዳጆቿን እያበዛች፣ ጠላቶቿን እየቀነሰች በአፍሪካ ያላትን አርዓያነት ለማስቀጠል እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሠራች ነው። ይህ ሥራዋም ውጤታማ ኾኗል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
