የመገጭ ምርቃት የወለደው አዲሱ የቱሪዝም ብሥራት!

7
የጎንደር የብርሃን ዘመን መገለጥ ጀምሯል። ለዘመናት በዐይኖች ብትታይም በልብ ማስተዋል እጦት የተረሳችው ከተማ በቅርቡ ትንሣኤዋ ተበሥሯል።
የአብያተ መንግሥታቷ መታደስ እና የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ነፍስ ዘርቷል። በቅርቡ የተመረቀው የመገጭ ግድብ ደግሞ የዘመናት የውኃ ጥሟን ሊቆርጥ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ሊያሳልጥ ጫፍ ደርሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መገጭ 19 ዓመት ሙሉ ሕዝብ በውኃ ጥም እየተሰቃየ መጠናቀቅ ያልቻለ እርግማን እንደነበር ገልጸዋል። ግድቡን በማጠናቀቅ ወደ በረከት መቀየር ተችሏልም ነው ያሉት።
ልክ እንደ ጎርጎራ የቱሪዝም መዳረሻ መኾን የሚችሉ ሆቴሎች እና ሎጂዎች የመገጭ ግድብ አካባቢ እንዲገነቡም ጥሪ አቅርበዋል። ጎንደር ገብቶ መውጣት ብቻ ሳይኾን እረፍት ማድረግ እንዲቻልም ኢኮ ሪዞርቶች እንዲገነቡም አሳስበዋል።
የጎንደር የቱሪዝም መዳረሻ ይበልጥ እንዲያድግም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት።
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቅጣጫ በመቀበል ወደ ሥራ ለመግባት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጥረት ማድረግ ጀምሯል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ የመገጭ ግድብ ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ለከተማዋ የኢኮ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሆቴሎች እና ሪዞርቶች በአካባቢው እንዲገነቡ ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም ተናግረዋል።
ግድቡ ከመስኖ ልማት ባሻገር የመናፈሻ እና የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚኾንም ገልጸዋል። የቱሪዝምን ቆይታ በማራዘም ለጎንደር ከተማ ሌላ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚኾንም አንስተዋል። ጥናት ላይ በመመሥረት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት በመኾን በግድቡ አካባቢ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች እንዲገነቡ ይሠራልም ነው ያሉት።
በመስኖ ካናሉ የሚለሙ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በአካባቢው ለሚገነቡ ሆቴሎች ግብዓት እንደሚኾኑም ጠቁመዋል። የከተማ እና የገጠር ትሥሥርን እንደሚፈጥርም ነው ያነሱት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቅጣጫ በመከተል ባለሃብቶች በአካባቢው መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና የተለያዩ ሆቴሎችን እንዲገነቡ ይሠራልም ነው ያሉት።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሩሲያ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት እንደምትደግፍ አስታወቀች።
Next article” ግጭት ሕዝብን የሚያጎሳቁል በመኾኑ ሰላምን መርጠናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች