
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል። የክልሉ እሴቶችም ተጎድተዋል። በእርግጥ እሴቶችን አክብረው እና የሕዝብን መጎዳት አስበው ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሕዝብን ለመጥቀም የሚጥሩት ብዙ ናቸው።
ችግሩን የተገነዘቡ ሰላምን እየመረጡ ወደ ሕዝባቸው እየተመለሱ ነው። ዳሩ ግን አሁንም ሰላምን የገፉ እና በግጭት ውስጥ መቆየት የሚፈልጉ አሉ።
እነዚህ ታጣቂዎች ለክልሉ መልካም ነገር ከማይመኙ እና በኢትዮጵያ ጥላቻ ከሰከሩ አካላት ጋር ተጣምረው ሌላ የጥፋት መስመርን እየተከተሉ ይገኛሉ።
አሁን የአማራ ክልል ሕዝብ በውስጡ ሲያብላላው የነበረው አይቶ ችሎ ማለፍን በቃኝ ብሏል። በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የዝምታው ቆፈን ተገልጦ በቃን ሰላም ስጡን እያለ ይገኛል።
በስሁት ትርክት ከጠባቂው እና ከጋሻው ከመከላከያ ሠራዊት ሊያጣሉት የከጀሉትን ተረድቷቸዋል። ከሰሞኑ የአማራ ክልል ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ደግፎ፣ የውጭ ባዕዳን እና የውስጥ ባንዳን አውግዟል። ባንዳን እና ባዕዳንን በጽናት እንደሚታገልም ገልጿል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የተካሄዱ ሰልፎችን አስመልክተው ባስተላለፊት መልዕክት የክልላችን ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ለክልላችን ጸጥታ አካላት ተጋድሎ፣ ለኢትዮጵያ ሀገራችን መጽናት ያለውን ድጋፍ በአንድነት በአደባባይ ወጥቶ ገልጿል ብለዋል።
የሕዝባችን እውነተኛ አንጡራ ፍላጎቱ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት እና ልማት የተረጋገጠበት ሀገር እና ክልል መፍጠር ነው። የተካሄደው ከፍተኛ ትዕይንተ-ሕዝብ በተግባር ያረጋገጠው ይህንኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለሀገራችን አንድነት ያለውን የማይናወጥ አቋም በድጋሜ የገለጸበት ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነት ክብራችን፣ ጀግንነት መጠሪያችን፣ ነጻነት መለያችን ነው። ይኸው ነጻነታችን በየዘመኑ በነበሩት ትውልዶች በተከፈለ ክቡር መስዕዋትነት የተገኘ ድል ነው።
ዛሬም ቢኾን ታሪካችን በኅብረት ጠብቀን፣ ነጻነታችን አጽንተን፣ በልጇቿ ብርቱ ጥረት የበለጸገች፣ የተከበረች እና የታፈረች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በጋራ መሥራት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ ለሠላም መሥፈን እና ለሕግ የበላይነት መከበር ያለውን የጸና አቋም በሠለጠነ አኳኋን በአደባባይ ወጥቶ ለሰጠው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
