“አፍሪካ በአንድ ድምጽ እየተናገረች በዓለም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለባት” የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

16

 

12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም “በአፍሪካ ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እና ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ” በሚል መሪ መልዕክት በባሕርዳር እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው በፓናል ውይይት የተሳተፉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለእኛ ለአፍሪካውያን ትብብር ያስፈልገናል ብለዋል። ካልተባበርን ከውጭ የሚመጣውን ተጽዕኖ መቋቋም አንችልም ነው ያሉት። ትብብር ኀይል ነው፣ የተፋጠነ ትብብር አስፈላጊ እና ወሳኝም ነው ብለዋል።

በጣና ፎረምም ኾነ በሌሎች ጉባኤዎች ላይ የምናነሳቸው ሃሳቦችን መተግበር እና ውጤታማ ማድረግ ያስፈልገናል ነው ያሉት። ራሳችንን ለመጠበቅ ጥምረት ያስፈልገናል ብለዋል።

አፍሪካውያን ወሳኝ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎቻቸውን ማሳተፍ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ በሰጥቶ መቀበል የተቃኘ ነው፣ አፍሪካም ይሄን ታሳቢ በማድረግ መሥራት አለባት ነው ያሉት።

የጸጥታ እና የደኅንነት ችግር አሳሳቢ ናቸው፣ ይህ ደግሞ አሰልቺ ነው ብለዋል። አህጉራዊ ተቋሞቻችን ጠንካሮች አይደሉም፤ ለዚያም ነው የአህጉሪቱን ችግር እየፈቱ ያልኾኑት ነው ያሉት። ውስጥን ማየት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአፍሪካን ኅብረት ወጪ መሸፈን ሳይችሉ ተቋሙ የአፍሪካን ችግር ሊፈታ አይችልም፤ ይሄን ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል። አፍሪካ የራሷን ወጪ መሸፈን ትችላለች፣ የራሷን ችግርም በራሷ መፍታት ትችላለች ነው ያሉት።

የአፍሪካን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ከአፍሪካ ሀገራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን እያስተሳሰረች ነው፣ ትስስሩ ፈጣን እንዲኾን ግን ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

አፍሪካ በአንድ ድምጽ መናገር ስትጀምር እና አንድነቷን ስታጠናክር በጸጥታው ምክር ቤት ቦታ ይኖረናል ነው ያሉት። አፍሪካ በአንድ ድምጽ እየተናገረች በዓለም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለባት ብለዋል። በአንድ ድምጽ ስንናገር ተደማጭነታችንም ከፍ ይላል ነው ያሉት።

አፍሪካ አንድነቷን ስታረጋግጥ እና በአንድ ድምጽ ሳትናገር ቦታውን ብታገኘውም ትክክለኛ ድምጿ አይሰማበትም ብለዋል። ወጣቶች ቁርጠኛ ከኾኑ አፍሪካን መለወጥ እንደሚችሉም ተናግረዋል። የአፍሪካ ተስፋዋ ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሰላም እና ጸጥታ ሳይኖር የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር አይችልም” የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን
Next articleየአማራ ክልል መሬት ቢሮ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ትግበራ ፕሮጀክትን ለመፈጸም ከአጋር ተቋማት ጋር ተፈራረመ።