“በምጽዋ ወደብ የተላከ የአንድ መጠነኛ ሀገር ትጥቅ ሊኾን የሚችል መሣሪያ ተቆጣጥረናል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

75

 

119ኛው ዓመት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው። የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ 119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት እንኳን ለ119ኛው የመከላከያ ሠራዊት የምሥረታ ቀን አደረሳችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከሚባሉ ሀገረ መንግሥታት መካከል አንዷ እንደኾነች ታሪኳ ይናገራል ብለዋል። ዕድሜ ጠገብ ተቋማትን ከገነቡ ሀገራት ተርታም ትመደባለች ነው ያሉት። 119 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያ ከገነባቻቸው ተቋማት ውስጥ ቀዳሚ ሊባል የሚችል አንጋፋ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ለ119 ዓመታት የውጭ ጠላት እና ሀገር አፍራሽ ባንዳዎች ጋር እየተዋጋ ሀገር አቆይቷል ነው ያሉት።

መከላከያ ሠራዊት የሀገረ መንግሥት ሥርዓት እና የአንድ ሀገር መኖር አለመኖር የሚወስን የሀገር ሕልውና ምሰሶ መኾኑን ገልጸዋል። በዲጅታላይዜሽን ዘመን መከላከያ ሠራዊትን እናፈርሳለን፤ የሽግግር መንግሥት እናመጣለን የሚሉ ደፋር ባንዳዎች ተፈልፍለዋል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ እነዚህ ከተቻላቸው የሀገሪቱን ምሰሶ አፍርሰው ሀገር ለማፍረስ የከጀሉ ገንጣይ እና ሽብርተኛ የባዕድ ተልዕኮ ተሸካሚዎች ናቸው ብለዋል።

በዚህ ዓመት ከግብጽ እስከ አስመራ የተቀናጀው ጠላት መላላክ የተጠናወተውን ሕወሃት በመላክ በሀገሪቱ የሰሜኑ የተለያዩ ክፍሎች ጦርነት የከፈተ ቢኾንም ራሱ በከፈተው ጦርነት ‘እንዳልነበር ተደርጓል’ ነው ያሉት።

በምጽዋ ወደብ የተላከላቸውን የአንድ መጠነኛ ሀገር የጦር ትጥቅ ሊኾን የሚችል የጦር መሣሪያ መከላከያ ሠራዊቱ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። ጠላቶች ያሰቡት ሳይኾን ቀርቶ ፍላጎታቸው መክኗል ነው ያሉት።

መከላከያ ሠራዊቱ ተዳክሟል፤ ከገፈተርነው ይወድቃል ብለው በተነኮሱ ጊዜ ለመከላከያ ሠራዊቱ የተመኙትን ተጎንጭተው የትግራይን ንብረት ጭነው መንደፈራ ገብተዋል፤ አራተኛው ዙር ‘በዘራችሁ አይድረስ’ በእነሱ ላይ ደርሶባቸዋል ነው ያሉት የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

119ኛውን የሠራዊት ቀን ስናከበር ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ ለእኛ የደረሰችውን ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት እና ሕዝቦች ጋር በወንድማማችነት እና በመልካም ጉርብትና ለመኖር ጽኑ ፍላጎት ያላት ቢኾንም በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል ኾኖብናል ነው ያሉት።

የዓባይ ውኃ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋ፤ ቀይ ባሕር እኛ ኢትዮጵያውያንም ጭምር እንድንገለገልበት ፈጣሪ ያበጀው ባሕር ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ የኢትዮጵያ መንግሥት እና መከላከያ ሠራዊት ከሁለቱ ውኃዎች ኢትዮጵያ የምታገኘውን ጥቅም ከማስከበር ውጪ አማራጭ የላቸውምም ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#የድል-ሠራዊት #አሚኮ #Ethiopia #መከላከያ
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት የሚያልፍ እውነተኛ የድል ሠራዊት ነው” የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ
Next article“ሰላም እና ጸጥታ ሳይኖር የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር አይችልም” የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን