
119ኛው ዓመት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተገኙበት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በዚህ ወቅት በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንዲሁም የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ በተለያዩ የግዳጅ ግንባሮች ለሚገኙ ውድ የሠራዊቱ አባላት በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ለሀገር እና ለወገን ዘብ ከመቆም የበለጠ ታላቅ ክብር የለምና ለምትከፍሉት እስከሕይወት የደረሰ ውድ መስዋዕትነት በከፍተኛ ሀገራዊ አክብሮት በዚህ ታሪካዊ ቀን ላቅ ያለ ምሥጋና አቀርባለሁ ነው ያሉት።
የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ መልዕክት ሲከበር በጽናት እና በጀግንነት የታነጸው ሠራዊት የሀገርን ሕልውና የተፈታተኑ በርካታ ችግሮችን ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ነጻነት እና ታሪካዊ ኩራት በተግባር ያስመሰከረ እውነተኛ የድል ሠራዊት በመኾኑ ነው ብለዋል።
የድል ሠራዊት ማለት በጦር ግንባር ጠላትን መክቶ ከመመለስ ባሻገር ሀገሩን እና ሕዝቡን ለሁለንተናዊ ድል፣ ለዘላቂ ሰላም እና ለብሩህ ዕድገት የሚያበቃ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም እና ራዕይ ያለው ሠራዊት ማለት መኾኑን ገልጸዋል።
በመኾኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት አልፎ ድልን የተቀዳጀ፤ ሀገርን ለሁለንተናዊ ከፍታ የሚያበቃ እውነተኛ የድል ሠራዊት ነው ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ በሚታሰብበት ዕለት ሀገሪቱ በርካታ ፈተናዎችን እና ማዕበሎችን ተሻግራ ይበልጥ በተደላደለ እና አስተማማኝ መሠረት ላይ ኾና ወደ ታላቅነቷ የምትገሰግስበት ታላቅ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።
ለአፍታም ቢኾን ሳይናወጥ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የሕዝቡን ሰላም ዋነኛ ተልዕኮ አድርጎ የተነሳው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በከፈለው ተጋድሎ ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖሩ ዓበይት ድሎችን አስመዝግቧል ነው ያሉት።
የሀገሪቱን ሕልውና ለማፍረስ ከውስጥ እና ከውጭ የተሸረቡ አጥፊ ሴራዎችን በበሰለ ስትራቴጂያዊ አመራር፣ በላቀ ወታደራዊ ሥነ ምግባር፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና በሚደነቅ የውጊያ ብቃት መክቶ በማክሸፍ የሀገሪቱን ዳር ድንበር እና የሕዝቡን አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቁንም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በጦር ግንባር ከተቀዳጀው የድል አክሊል ባሻገር የቀጣናውን ሰላም በማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና በችግር ጊዜ ፈጥኖ በመድረስ እውነተኛ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር ማረጋገጡንም ገልጸዋል።
በተካሄደው ጥልቅ የለውጥ ሥራ ሠራዊቱ በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ምኅዳሮች ያለው ሁለንተናዊ የውጊያ እና የደኅንነት አቅም በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
