“መሬትን በአግባቡ ካልተጠቀምን ለትውልድ የምናስተላልፈው ሃብት የለንም” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

16

 

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የገጠር መሬት አጠቃቀም እና አያያዝ ዳይሬክቶሬት የተቀናጀ የተስማሚነት የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ትግበራ ፕሮጀክት ላይ ውይይት አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ክልሉ በግጭት ውስጥ ኾኖ አርቆ በመመልከት እየሠራ ነው ብለዋል።

በ25 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ እና በአምስት ዓመቱ የስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ግብርናን ማዘመን፣ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትልቅ ትኩረት ተሠጥቷል ነው ያሉት።

የክልሉ ግብርና የሚዘምነው፤ ምርት እና ምርታማነት የሚረጋገጠው የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት በዕውቀት እና በሳይንሳዊ መንገድ ሲመራ ብቻ ነው ብለዋል።

መሬት ቢሮ ተዘንግቶ የነበረውን ዘርፍ እንደገና ለማጠናከር እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። መሬትን በአግባቡ ካልተጠቀምን ለትውልድ የምናስተላልፈው ሃብት የለንም ነው ያሉት።

መሬት መሥጠት የሚጠበቅባትን ጥቅም እንድትሰጥ መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ወደ ምርት ማስገባት ያስፈልጋል፤ ለውጤታማነት በትጋት እና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ተቋሙ የገጠር ኮሪደር ልማትን እና የቀበሌ ማዕከላትን ማዘመን፣ የመሬት አጠቃቀምን ማስተካከል እና የከተማ መሬት ካዳስተር ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ለማጽናት ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍሏል” ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ
Next article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት የሚያልፍ እውነተኛ የድል ሠራዊት ነው” የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ