“ስንከፋፈል እንበዘበዛለን፣ እንድ ኾነን በአንድ ድምጽ እንናገር ” የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ

14

 

12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም “የሰላም መንገዶች በአፍሪካ፦ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የጣና ፎረም በነጻነት ስለ አፍሪካዊ ጉዳዮች እንድንወያይ የሚያደርግ ነው ብለዋል። እዚህ የተገኘነው ሱዳን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ባለበት ወቅት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሱዳናዊያን ዋጋ እየከፈሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባሸገር በሳህል ቀጣና የሚገኙ ታጣቂዎች ሀገራትን እየረበሹ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በዚህ ሁኔታ ልጆች እየተማሩ አይደለም ነው ያሉት። ለልጆቻችን ተስፋ እየሰጠን ያለነው የጦር መሣሪያ ነው፣ ይህ ለትውልድ የሚጠቅም አይደለም ብለዋል።

ሰላም እና ደኅንነትን በአሕጉራችን አፍሪካ ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት። ሽምግልናን የዘር ጭፍጨፋ ከተፈጸመ በኋላ መጠቀም ትርጉም የለውም፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያን ወደ ጠንካራ ቅድመ እርምጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል። የአፍሪካን ሃብት እሴት መጨመር እና አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ለግጭት መንስኤ ይኾናሉ ብለዋል።

ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መኾናቸውንም ተናግረዋል። ችግሮችን በውይይት እና በድርድር መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። ስንከፋፈል እንበዘበዛለን፣ እንድ ኾነን በአንድ ድምጽ እንናገር ነው ያሉት።

አፍሪካዊ አቋም መያዝ እና ድምጽን በጋራ ማሰማት እንደሚገባም አመላክተዋል። አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። አፍሪካ በአንድ ድምጽ ልትናገር ይገባል፣ የራሷ መንገድም ሊኖራት ይገባል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ሰላም ደግሞ አንድነትን ያመጣል ብለዋል። ሰላም ያስፈልገናል፣ ያለ እርቅ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት። በየትኛውም የአህጉሪቱ ክፍል ያሉ ታጣቂዎች መሣሪያቸውን ጥለው ወደ ምክክር እንዲመጡ እና እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ እንዲያስቡም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።

የሰውነታችን አካል ተነጣጥለው መሥራት እንደማይችሉ ሁሉ አፍሪካውያን ብቻቸውን ምንም ማድረግ አይችሉም ነው ያሉት። በጥምረት እና በአንድነት መሥራት አለብን፣ ወደ ጦርነት ከመሄድ መቆጠብም አለብን ብለዋል።

የጣና ፎረም በግልጽ እና በጥልቀት የምንነጋገርበት መድረክ ነው ብለዋል። ሰላም የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚፈልግም ተናግረዋል። አፍሪካዊ ስጋቶችን ማስወገድ እንደሚገባም አመላክተዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“አፍሪካ ጠንካራ ድምጽ ሊኖራት ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ተለዋዋጭ በኾነው ዓለም ውስጥ ጠንካራ አፍሪካዊ ኅብረት እና ግልጽ ዓላማ ሊኖረን ይገባል” አምባሳደር ሰልማ ማሊካ