“አፍሪካ ጠንካራ ድምጽ ሊኖራት ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

11

 

12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም “በአፍሪካ ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እና ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንኳን ወደ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ፣ እንኳን ወደ ዓባይ ምንጭ ባሕር ዳር በደህና መጣችሁ ብለዋል።

የጣና ፎረም ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም የሚመክር መኾኑንም ተናግረዋል። ለአፍሪካ ችግር የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ግጭት ሀገርን እና ሕዝብን እንደሚጎዳም ተናግረዋል።

አፍሪካ ጠንካራ ድምጽ ሊኖራት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን በትብብር እውን ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ጉዳይዋ መኾኑንም ተናግረዋል። ሰላማዊ መንገድን ከመረጡ አካላት ጋር ሁሉ ለመወያየት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። አፍሪካ መር ውይይት የሚያሳየውም ይህንኑ ነው ብለዋል።

ሰላም የሚጸናው ተወያይ ወገኖች በቃላቸው ሲጸኑ መኾኑንም ገልጸዋል። የእኛ ዘላቂ ፍላጎት ሰላም ዘላቂ ብልጽግና እንዲያመጣ ነው ብለዋል። ሰላም እና ብልጽግና የመደመር መንግሥት መርህ ናቸው፤ አንድነትን እናጠናክራለን፣ ራሳችን እናመርታለን፣ በራሳችን እንወስናለን ነው ያሉት።

አንድነት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባቱንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እምርታን ለማረጋገጥ እየሠራች መኾኗንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኀይል አቅርቦትን ለጎረቤቶቿ እየሰጠች መኾኗን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራች መኾኗንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ሥራ እየሠራች መኾኗንም ገልጸዋል። ለቀጣዩ ትውልድ መዘጋጀት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ኤአይ ዩኒቨርሲቲ እየገነባን ነው ብለዋል።

130 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት ሀገር የባሕር በር ማግኘት የሕልውና ጉዳይ ነው፣ እያንዳንዱን ጉዳይ በሌሎች ይሁንታ ማለፍ የደኅንነት ዋስትናን እንደማይሰጥ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ሰላማዊ አማራጭን በማስቀደም እየሠራች ነው ብለዋል።

አፍሪካውያን ሰላምን ማዝለቅ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ይገባናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከሏንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ32ን ታዘጋጃለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ከእኛ ጋር ኾኖ ማዘጋጀት አለበት፣ የአፍሪካን አንገብጋቢ ጉዳዮች ለዓለም እናስተጋባ ነው ያሉት።

አፍሪካውያን በአንድነት ስለ አህጉራቸው መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ጥንካሬያችን ያለው በጋራ አንድነታችን ላይ ነው” የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ
Next article“ስንከፋፈል እንበዘበዛለን፣ እንድ ኾነን በአንድ ድምጽ እንናገር ” የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ