
12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም “የሰላም መንገዶች በአፍሪካ፦ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጋናው ፕሬዝዳንት እና የጣና ፎረም ሠብሣቢ ጆን ድራማኒ ማሃማ እንኳን ወደ ዓባይ መነሻ ባሕር ዳር በሰላም መጣችሁ ብለዋል። እዚህ የተገናኘነው ስለ አፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ለማውራት ነው ብለዋል።
ጉባኤው ጥልቅ ግላዊ እና ተቋማዊ ትርጉም እንዳለውም ገልጸዋል። የጣና ፎረም ለግልጽ ውይይት፣ ለስትራቴጂካዊ በጎ ዕይታ እና ለሉዓላዊ መፍትሔዎች የሚያገለግል እውነተኛ እና አፍሪካዊ ቦታ መኾኑን ገልጸዋል።
የጣና ፎረም ባለፉት ዓመታት ስለ አህጉራችን ሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ለመወያየት ልዩ መድረክ ኾኖ አገልግሏል ነው ያሉት። በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ሊገነባ የሚችለው በአፍሪካውያን ባለቤትነት እና በአህጉራዊ ውሳኔ ሰጪነት መሠረት ላይ ብቻ ነው ብለዋል።
የዚህ ዓመት መሪ የፎረሙ መልዕክትም የዘመናችንን ዋና ፈተና ቀጥታ የሚመለከት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የዓለም አቀፉ ሥርዓት ትልቅ መዋቅራዊ ለውጦች እያጋጠሙት መኾኑን ገልጸዋል።
የከረረ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር፣ ለስትራቴጂካዊ ወሳኝ ማዕድናት የሚደረግ ውድድር፣ ያልተረጋጋ የዓለም አቀፍ ሁኔታ እና የቴክኖሎጂ ተጽዕኖዎች የዓለምን ሥርዓት እየዘወሩት መኾናቸውንም አንስተዋል።
በዚህ የዓለም ሁኔታ ውስጥ አፍሪካ ተመልካች ኾና መቅረት አትችልም፤ አህጉራችን የውጭ ኀይሎች መፋለሚያ እንድትኾን መፍቀድ የለብንም ነው ያሉት።
ሰላም የመጨረሻ ግባችን ከኾነ፣ የተለያዩ ተሞክሮዎቻችን፣ ተቋማዊ ፍላጎቶቻችን እና የሕዝብ ቁጥር እና ጥንካሬያችን ወደዚያ ግብ ለመድረስ በርካታ መንገዶችን ያቀርቡልናል ብለዋል።
ዘላቂ ደኅንነት ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ይፈልጋል፤ ዘላቂ ሰላም ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ይጠይቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከጥገኝነት ወደ ተሻለ ዕድገት መጓዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሕዝብ በኢኮኖሚ በተገለለበት ቦታ የተረጋጋ ሰላም አይኖርም፤ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ልንሻው የሚገባን የመጀመሪያው እና ወሳኝ የደኅንነት ክልላችን ነው ብለዋል።
እየጨመረ በመጣው ባለብዙ-ዋልታ ዓለም ውስጥ፣ ጥንካሬያችን ያለው በጋራ አንድነታችን ላይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በባለብዙ ወገን ሥርዓት እና በዓለም አቀፍ አሥተዳደር ተቋማት ላይ ፍትሐዊ ማሻሻያ እንዲደረግ በጋራ መጠየቅ አለብን ነው ያሉት።
ወደ ውጭ የምናደርገው ግንኙነት እንዳለ ኾኖ ዋናው ስትራቴጂካዊ ትኩረታችን ውስጣዊ መኾን አለበት ብለዋል። ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
