
12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም “የሰላም መንገዶች በአፍሪካ፦ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ወደ ባሕርዳር ስለመጣችሁ ደስ ብሎኛል ነው ያሉት።
ጣና ፎረም የአፍሪካ መሪዎችን በአንድ አሠባሥቦ ስለ አፍሪካ የሚመከርበት መድረክ መኾኑን ገልጸዋል። ጣና ፎረም ሲመሠረት መሠብሠቢያ ባሕር ዳርን መምረጡን አስታውሰዋል።
ፎረሙ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች ለመስጠት የሚደረግ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሰላም የሚሰፍነው በአዋጅ አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላም የሚሰፍነው ተግባራዊ ርምጃዎች ሲኖሩ መኾኑን አመላክተዋል። ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ መኾናቸውን እንገነዘባለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ብሎም የኢትዮጵያን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ፎረሙ ለሰላም እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ እናደንቃለንም ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ለውይይት የተመቸች፣ ጥልቅ የኾነ ታሪክ እና ተፈጥሮ ያለባት ከተማ ናት፤ ባሕር ዳር የጥንታዊ ገዳማት እና በርካታ ቅርሶች መገኛ መኾኗንም ተናግረዋል። ባሕር ዳር የምትታወቀው በትምህርት ከተማነቷ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ባሕርዳር የሥብሠባ እና የጉብኝት ማዕከል እንድትኾንም እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል እንዲህ አይነት ጉባኤ በማዘጋጀቱ ኩራት ይሰማናል፤ ወደፊት መስተንግዶው እየላቀ፣ መድረኩም የበለጠ እያደገ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ወደ ባሕር ዳር መምጣታችሁ ትርጉም ያለው ትስስር ለመፍጠር ያስችላልም ነው ያሉት። እንግዶች በባሕር ዳር እና አካባቢው ያለውን ሀብት እንዲጎበኙ፣ የክልሉን ባሕል እና እሴት እንዲያዩም ጥሪ አቅርበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
