
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በክልሉ በምዕራብ አማራ ቀጣና በ38 ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የገጠር እና የከተማ መሬትን በአግባቡ ለመያዝ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። በተሠራው ሥራም በገጠሩ ዘርፍ አበረታች የግብርና ልማት ሥራ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በተለይ አርሶአደሮች የመሬት የማረጋገጫ ድብተር ማግኘታቸው ብድር እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል። ብዙ የመልካም አሥተዳደር እና የብልሹ አሠራር ምንጭ የሚከሰቱት ከመሬት አሥተዳደር መኾኑንም አንስተዋል።
መሬትን በአግባቡ ሥርዓት ማስያዝ እና ዘመናዊ በኾነ መንገድ መምራት፣ መልካም አሥተዳደርን ማስፈን እና ሀብትን በአግባቡ ቆጥሮ መያዝ ይገባልም ብለዋል። ዘርፉ ትልቅ የጉቦ ምንጭ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ሳህሉ የሚመለከታቸው አካላት አሠራራቸውን ውጤታማ በማድረግ ቅቡልነት ያለው ሥርዓት መገንባት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ዘርፉ የዜጎች የቅሬታ ምንጭ ከመኾን ወጥቶ ሥርነቀል ለውጥ ማምጣት ይገባዋልም ነው ያሉት። በዚህም ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓት (ካዳስተር) ቴክኖሎጂ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በ14 ከተሞች ሲከናወን መቆየቱን አውስተዋል። በዚህም በስምንት ዓመት 118ሺህ 305 ቁራሽ መሬት በዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት ውስጥ መመዝገቡን እና መረጋገጥ መቻሉንም ነው የገለጹት።
የከተማ መሬት ምዝገባ እና አሥተዳደር ሥርዓትን በዘመናዊ መንገድ በመምራት፤ አሠራርን በማስተካከል እና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የከተሞች ልማት እንዲፋጠን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የከተማ መሬት ሀብት በአግባቡ በመመዝገብ ለታለመለት ዓላማ ማዋል፤ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር መገንባት ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ነው ያሉት። አሁን ላይ በክልሉ ከነባሮች 66 ከተሞች በተጨማሪ በምዕራብ አማራ በ38ከተሞች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሠራርም ይዘረጋል ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_14_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
