ጀምሮ አለመጨረስን ከኢትዮጵያ መልክነት የፋቁ ፕሮጀክቶች

15

 

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት እውን ለማድረግ መንግሥት ለታላላቅ የልማት እንቅስቃሴዎች የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ቢኾንም የፕሮጀክቶች መዘግየት ግን በቀላሉ የማይታይ ተግዳሮት ኾኖ ቆይቷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተያዘለት የአምስት ዓመት ዕቅድ በተጨማሪ ዘጠኝ ዓመታትን ጠይቆ በ14 ዓመቱ ተጠናቅቋል።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት እንድትሸጋገር፤ የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትኾን ካደረጉ ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚው ኾኗል።

የመገጭ የመስኖ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በ19 ዓመቱ ተጠናቅቋል። ይህ መጓተት ሀገሪቱ የነበራትን የመፈጸም አቅም ድክመት፣ የሀብት ማባከን፣ የክትትል ክፍተት እና የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በግልጽ ያመላክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቀድሞው አሠራር ፕሮጀክቶችን በማጓተት የሕዝብን እንግልት እና የፋይናንስ ኪሳራ የሚያባብስ እንደነበር ገልጸዋል።

ለዕድገት ወሳኝ የኾኑ ፕሮጀክቶችን ማጓተት የሕዝብን ጥያቄ መናቅ እና የሀገርን ተስፋ ማጨለም መኾኑንም በተለያዩ መድረኮች ተናግረዋል።

ችግሩ የባለሙያዎች ወይም የኮንትራክተሮች ብቻ ሳይኾን እምቅ አቅምን ወደ ውጤት የመቀየር ድርጅታዊ እና ተቋማዊ ክፍተት እንደኾነም አስረድተዋል። በዚህም በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገቡ የልማት ስብራቶችንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው ፈተና ያሉት ሉዓላዊ አቅም አለመደርጀትን ነው። ይህም ሥራን በራስ አቅም ጀምሮ እስከ መጨረሻው የማድረስ ውስንነትን ወይም 90 በመቶ ሠርቶ ቀሪውን 10 በመቶ ሌላ አካል እንዲጨርሰው የመጠበቅ ልማድን ያመላክታል።

ጨርሶ አለመጀመር ወይም ጀምሮ አለማጠናቀቅን ሌላኛው ፈተና በማድረግ ጠቁመዋል። ይህም ሃሳብን መሬት ላይ ባለማውረድ እና የሥራን ተከታታይነት ባለማረጋገጥ የሚፈጠር ስብራት ነው።

የመጨረሻው ፈተና ደግሞ ሥርዓታዊ ስልጡንነት ማጣት ሲኾን ይህም የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ በመናበብ፣ በመነጋገር እና በመደጋገፍ ሠርቶ ለማጠናቀቅ አለመቻል እንደኾነ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ይህንን የተዛባ አሠራር በመቀየር የተጀመሩ ሥራዎችን በፍጥነት እና በጥራት የማጠናቀቅ ጽኑ አቋም ይዟል ነው ያሉት።

ለዓመታት ታስረው የነበሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ፍጻሜ እንዲደርሱ መደረጉም የመፈጸም አቅምን ማጠናከር እና ብልሹ አሠራሮችን መታገል የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መኾኑን ያረጋግጣል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#AMECO #FinishingWhatWeStarted #Ethiopia
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_13_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአፍሪካውያን መሪዎች ስለ አፍሪካ፤ በውቢቷ ባሕር ዳር
Next article“የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማ እና አካባቢው ማኅበረሰብ የልማት ገጸ በረከት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ