
ጣናን እና ዓባይን ተንተርሳ በተፈጥሮ የተጎናጸፈችው የጣናዋ ንግሥት ባሕር ዳር ውበት ትልቁ መገለጫዋ እና መልኳ ነው። ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ባካሄደችው የኮሪደር ልማት አምራ፣ ደምቃ እና አሸብርቃ ትገኛለች።
የከተማዋን ውበት በአረንጓዴ ልማት ማሳመር ደግሞ ይበልጥ ማራኪነቷን አጉልቶታል።
ጣና እና ዓባይ ተስማምተው እቅፍ አድርገው በያዟት በዚህች አረንጓዴ ከተማ፣ የጥበብ እጆችም በውበት ላይ ውበት ደርበውላታል።
ይህ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ውበቷ ባሕር ዳርን የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላታል።
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካውያን መፍትሔን” አልሞ የሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ የሚካሄደው በዚህች ውብ ከተማ ነው።
አፍሪካውያን መሪዎች፣ ኘሬዝዳንቶች፣ ዲኘሎማቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጣና ዳርቻ ንጹሑን አየር እየተነፈሱ ለአሕጉሪቱ ሰላም እና እድገት የመፍትሔ ውይይት ያደርጋሉ።
የጣና ፎረም በዚች ሰገነት ከተማ መካሄዱ ከተማዋን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ መድረክ ከመኾኑም በላይ የከተማዋን ቱሪዝም በማነቃቃት የኮንፈረንስ ከተማ መናገሻ ያደርጋታል።
በእነዚህ ሁሉ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ የባሕር ዳር ማኅበረሰብ የሚያሳየው ጨዋነት፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ደግነት የከተማዋ ሌላው ደማቅ ገጽታ ነው። ባሕር ዳር ባለፉት ዓመታት የጣና ፎረምን በስኬት እንዳስተናገደች ሁሉ ወደፊትም የቱሪዝም፣ የኮንፈረንስ እና የስፖርት መናገሻነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በፎረሙ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ፍቅርን፣ሰላምን እና አንድነትን የምንሰጥበት እና ታሪካችንን በተግባር የምናረጋግጥበት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_13_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
