የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የውኃ ጥም ሊቆረጥ ይኾን?

13

 

ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ የሀገር ዋልታ እና ማገር ባለውለታዋ ጎንደር ከተማ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አብረዋት የዘለቁ የመሠረተ ልማት ችግሮች ነዋሪዎቿን እጅግ የፈተኑ ነበሩ።

የከተማዋ የአስፋልት መንገዶች በዕድሜ ብዛት የተጎራረዱ ኾነው ለተሽከርካሪ የማይመቹ እና ለዕይታ የማይስቡ ነበሩ። ታሪካዊ አብያተ መንግሥታትም የመፍረስ አደጋ ተደቅኖባቸው ቆይቶ ነበር።

ከከተማዋ ወደ አዘዞ የሚወስደው የአስፋልት መንገድም ሳይጠናቀቅ ለረጅም ዓመታት እየተጓተተ መዝለቁ እንዳለ ኾኖ በተለይ ደግሞ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጦት የነዋሪዎቿ የረጅም ዓመታት የቅድሚያ ቅድሚያ ጥያቄ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እነዚህ ሁሉ ታሪኮች እየተቀየሩ ነው። ጠባብ እና የተጎራረዱ የአስፋልት መንገዶቿ በኮሪደር ልማት ሰፍተው እና ተስተካክለው፣ አብያተ መንግሥታቶቿም በእድሳት እና በጥገና ሕይወት ዘርተው ከተማዋ አሸብርቃለች።

ከጎንደር አዘዞ የሚወስደው እና ለረጅም ዓመታት የተጓተተው የአስፋልት መንገድም 92 በመቶ እንደደረሰ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር ይህ ሁሉ ሲኾን አንድ ያልተመለሰ የነዋሪዎቿ ጥያቄ እስካሁንም አለ። እሱም የንጹሕ መጠጥ ውኃ ነው።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በንጹሕ መጠጥ ውኃ እጦት ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት በላይ እጅግ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፈዋል። ነዋሪዎች በየሰፈሩ ባሉ የሕዝብ የውኃ ቧንቧዎች ጀሪካኖች ደርድረው፣ ሴቶች እና ሕፃናት በብርድ እየተንቀጠቀጡ ወረፋ ለመጠበቅ ሲገደዱ ኖረዋል።

በየመኖሪያ ቤቶቹ የውኃ ቧንቧዎች የተዘረጉ ቢኾንም ነዋሪዎች ውኃ የሚያገኙት በወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ወር ሙሉ የሚያሳልፉት በትልልቅ ማጠራቀሚያዎች ውኃ ሞልተው በማስቀመጥ ነው። እንዲያም ኾኖ በቂ ባለመኾኑ በዙሪያው ባሉ ሸለቆዎች ወርደው ውኃ ለመቅዳት ይገደዳሉ። በዚህ መካከል በውኃ ብክለት ለጤና ችግር የሚዳረገው ነዋሪ በርካታ ነው።

ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሥራ ተጀመረ የተባለው የዛሬ 18 ዓመታት ገደማ ነበር። መገጭ ግድብ ተጀመረ ሲባል የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ ችግሩ መፍትሔ ያገኛል ብለው ተስፋ ሰንቀው ነበር። ኾኖም ለ18 ዓመታት መንግሥትን እየጠየቁ፣ ከውኃ ጥም ጋር እየታገሉ በትዕግስት ጠበቁ።

ዛሬ ያ የዘመናት የውኃ ጥማቸው ሊቆረጥ፣ የትናንቱ እንግልት እና አንድ ወር የውኃ መምጣትን መጠባበቅ ሊያበቃ ጫፍ ላይ መድረሱ እየተነገረ ይገኛል።

ከ18 ዓመታት ጥበቃ በኋላ የመገጭ ግድብ ለምርቃት በቅቷል። ይህ የመስኖ እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እጅግ ዘመናዊ በኾነ የውኃ ማጣሪያ እና ማሰራጫ መስመር አማካኝነት ቀጥታ ወደ ጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ቤት እንደሚደርስ ነው የተነገረው።

ለከተማዋ አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት መዘርጋቱ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በሁለንተናዊ የኑሮ ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ሌላኛው የጎንደር ሕዳሴ ይኾናል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#አሚኮ #መገጭ_ግድብ #የንጹሕ_መጠጥ_ውኃ #አማራ_ክልል

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_13_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየጣና ፎረም ተሳታፊ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ባሕር ዳር ከተማ መግባታቸውን ቀጥለዋል።
Next article“ሕዝቡ በውኃ እጥረት እየተቸገረ አንድ ፕሮጄክት ለዓመታት አለመጨረስ እርግማን ነበር” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)