
በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የተካሄደውን ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በማስመልከት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በመግለጫቸው የክልሉ ሕዝብ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች በነቂስ ወጥቶ የሀገርን ሉዓላዊነት እና አንድነትን የማረጋገጥ ጽኑ አቋሙን ማሳየቱን ገልጸዋል።
የሰልፉ ዓላማ በጥፋት አጀንዳ ተደራጅተው ሀገር ለማመስ የተንቀሳቀሱትን ሕገ ወጡ ሕወሃት፣ የጽንፈኛው ኀይል እና የላኪዎቻቸውን የሻቢያ እና ግብጽ እኩይ ሴራን ለማውገዝ መኾኑን አንስተዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝቡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ለክልሉ የጸጥታ አካላት ያለውን ጽኑ ደጀንነት እና አጋርነት በተጨባጭ ያረጋገጠበት መኾኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በታሪክም የውጭ ጠላቶችን እና የውስጥ ተላላኪዎችን ሴራ በአንድነት አክሽፈው ለዘመናት መኖራቸውን አስታውሰዋል።
አሁንም የጠላቶች ቅንጅት ከንቱ እንደሚቀር በአደባባይ መረጋገጡንም አስገንዝበዋል።
ሕዝቡ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ልማት እንዲፋጠን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ ከግድቡ እስከ ወደቡ የሚደረገውን የባሕር በር ጥረት ጨምሮ የሀገርን ልማት እና ዕድገት የሚያደናቅፉ ሴራዎችን በመበጣጠስ ከመንግሥት ጎን አብሮ ለመቆም ዝግጁ መኾኑ በሰልፉ በግልጽ ታይቷል ነው ያሉት።
በመጨረሻም ሕዝቡ ለሀገር መጽናት፣ ለሕዝቦች አንድነት እና ለጸጥታ ኀይሎች ላደረገው ድጋፍ እና ላስተላለፈው ግልጽ መልዕክት ምሥጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
