
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት የተጓዘባቸውን ሂደቶች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ከምክክሩ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስረከብ ሥራ ሠርቷል ብለዋል።
በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አሥተዳደር ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት እና በማደራጀት ለሚመለከታቸው አካላት ማስረከቡንም ጠቅሰዋል። ምክክሩ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል፣ መተማመን እንዲገነባ፣ አዲስ የፖለቲካ ባሕል
እና መድረክ እንዲፈጠር ያስቻለ እንደነበርም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ እና መዋቅራዊ ችግሮችን በመመካከር የመፍታት የፖለቲካ ባሕል እንዲያድግ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር እንዲቻል አበርክቶው የጎላ ስለመኾኑም በመግለጫው
ተነስቷል። በምክክሩ ሂደት አዲስ ማኅበራዊ ውል እና ጠንካራ ቅቡልነት ያላት ሀገርን ለመገንባት ጽኑ መሠረት የሚኾኑ ምክረ ሃሳቦች ተገኝተውበታል ነው ያሉት። በምክክሩ የተገኙ ውጤቶች ችግሮቻችን በመነጋገር፣ በጋራ ግንዛቤ እና በሕዝባዊ ተሳትፎ ለመፍታት የሚደረገው
ጥረት መሠረቶች ናቸውም ብለዋል ኮሚሽነሩ። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጡት 394 ምክረ ሃሳቦች ምክር ቤቱ በቀጣይ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ይኾናሉ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት አራት ዓመታት ከስምንት ወር
የተጣለበትን ኀላፊነት በሚገባ መወጣቱን ጠቁመው ስኬታማ እንዲኾን ለተሳተፉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበው የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡
በቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
