
በፍኖተ ሰላም ከተማ እና በጃቢጠህናን ወረዳ ነዋሪዎች የተቀናጀ የመከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ፣ እንዲሁም ጽንፈኝነትን እና ሥርዓት አልበኝነትን የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል። ሀገር ለማፍረስ የሚውተረተሩ ባዕዳ እና ባንዳዎችንም በዓደባባይ አውግዘዋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች “ለድል የተወለደው መከላከያ ሠራዊታችን አለኝታችን ነው” ብለዋል። አክለውም የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፉ ኀይሎችን ያወገዙ ሲኾን መንግሥት ሰላምን ለማስፈን እና የእነዚህን አካላት ሴራ ለማክሸፍ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግ አረገ ሕዝቡ ሀገርን በመጠበቅ እና ሠራዊቱን በመደገፍ አለኝታነቱን ማሳየቱን ገልጸው፣ የታሪካዊ ጠላቶችን አጀንዳ የተቀበሉ ባንዳዎችን ማውገዝ ተገቢ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ታሪካዊ ጠላቶች ሕዝብን ለመከፋፈል እና ሀገርን ለመበተን የሸረቡትን እኩይ ድርጊት መከላከያ ሠራዊቱ ማክሸፉን አስገንዝበዋል።
ጽንፈኝነት በባንዳዎች የሚቀነቀን የባዕዳን አፍራሽ አስተሳሰብ በመኾኑ ሁሉም በጋራ ሊታገለው እንደሚገባ እና የባዕዳን ሴራዎችን በማጋለጥ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚደረገውን ደጀንነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
