
የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ እና የሀገር ውስጥ ሰላምን፣ ልማትን እንዲሁም የባሕር በር ባለቤትነትን ጨምሮ ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስከበር ጽኑ አቋማቸውን የሚያሳይ ሕዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል። ነዋሪዎቹ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሚወስደውን
እርምጃ በመደገፍ፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ እና ለክልሉ የጸጥታ መዋቅር ደጀንነታቸውን አረጋግጠዋል፤ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማፍረስ የሚሠሩ አካላትንም አውግዘዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ እንደገለጹት ሕዝቡ በአደባባይ በመውጣት ለሠራዊቱ
ያለውን የማያወላውል ድጋፍ የገለጸ ሲኾን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ፀረ-ሰላም ኀይሎችም ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል። አቶ ዱባለ አክለውም መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጠብቆ ያቆየ፣ ከሀገር አልፎም በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጀግንነቱን ያረጋገጠ መከታ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሠራዊቱ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ውበት አዋሕዶ የያዘ «ትንሿ ኢትዮጵያ» በመኾኑ የክብራችን መገለጫ ነው፤ በተላበሰው ሕዝባዊ ባህሪ ምክንያትም በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ከሕጻናት እስከ አዋቂ እንደ ቤተሰብ ተጠግቶ ተቀባይነት አግኝቷል፤ ባለፉት ወራትም የትግራይ ሕዝብ
ለሠራዊቱ ያሳየው ታላቅ ድጋፍ እና እምነት የዚሁ ሕዝባዊነቱ ማሳያ ነው ብለዋል። የግብጽ እና የሻዕቢያን ተልዕኮ ተቀብለው በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈቱ ጽንፈኛ ኀይሎች በሠራዊቱ የማይበገር ክንድ መደቆሳቸውን እና ለዚሁም ሕዝቡ ላሳየው ደጀንነት እና ድጋፍ አወድሰዋል።
ባለፉት ዓመታት ሠራዊቱ ውሥብሥብ ፈተናዎችን አልፎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና መዋቅር በመደራጀት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት የመጠበቅ አቅሙን በተግባር ያረጋገጠ ብሔራዊ ኀይል ኾኗልም ነው ያሉት። በመጨረሻም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አኩሪ ድል ላስመዘገቡት
ለመከላከያ ሠራዊት ክፍሎች፣ ለክልሉ የጸጥታ ኀይሎች እና ለደኅንነት መዋቅሩ በደሴ ከተማ ሕዝብ ስም የላቀ ምሥጋና እና ክብር አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
