ለጥንቃቄ፦ የወባ ስረጭት ምን ደረጃ ላይ ነው?

6
ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2019 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅቱ የወባ በሽታ በከፍተኛ ኹኔታ ኅብረተሰቡን የሚፈትንበት ነው። የአማራ ክልልም የወባ ስርጭት ከሚፈትናቸው አካባቢዎች መካከል ይገኛል።
✍️አኹን ላይ የወባ ስረጭት ምን ደረጃ ላይ ነው? ​በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ቅናሽ አለው። በክልሉ ጤና ቢሮ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም አሥተባባሪ ዳምጤ ላንክር ወቅቱ በሽታው በከፍተኛ ኹኔታ የሚተላለፍበት ነው እና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።
​ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ባለው ጊዜ ከፍተኛ የበሽታው መተላለፊያ ወቅት በመኾኑ በየሳምንቱ የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ​እስካኹን በወረርሽኝ ደረጃ የተመዘገበ ወረዳ ባይኖርም የበሽታው ጫና ግን ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ምዕራቡ የክልሉ ቀጠና 90 በመቶ የሚኾነውን የወባ ተጋላጭ መኾኑን ጠቁመዋል። በክልሉ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 40 ያህሉ 62 በመቶ የሚኾነውን የታማሚ ቁጥር የሚሸፍኑ ይሸፍናሉ። ደራ፣ ጓንግዋ፣ ቻግኒ ከተማ፣ ዚገም፣ ጃዊ እና አየሁ ጓጉሳ ከፍተኛ ተጋላጭ ከኾኑት መካከል ይጠቀሳሉ። ደራ ወረዳ ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ይዟል ነው ያሉት።
✍️ወደ ወረረሽኝ እንዳያድግ ምን እየተሠራ ነው?
#በ17 ወረዳዎች በሚገኙ 419 ቀበሌዎች የቤት ውስጥ የወባ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ሲኾን እስካኹንም 70 በመቶው ተጠናቋል።
#በሽታው በከፍተኛ ኹኔታ በሚታይባቸው አካባቢዎች በሙሉ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
#የመኝታ አጎበር አጠቃቀምን የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ ነው። የቀረበው የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበሮች ጥያቄ እንደደረሰም አጎበር ላላገኙ አካባቢዎች ይሠራጫል።
#ሕመምተኞች ፈጣን ምርመራና ሕክምና የሚያገኙበት ኹኔታ እየተመቻቸ ነው።
#የመድኃኒት እጥረት እንዳይከሰትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
✍️ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቃል?
#የሕመም ስሜት ሲሰማ በፍጥነት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ መመርመር እና የታዘዘን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ።
#ያለ ሕክምና ምርመራ ከመድኃኒት ቤቶች መድኃኒት ከመግዛት መቆጠብ።
#እንደ ጀሪካን፣ ጣሳ እና የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን በማዳፈንና በማፍሰስ የትንኝ መራቢያዎችን ማጥፋት።
#የመኝታ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እና በአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች ላይ በነቃ መሳተፍ።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጎዛምን ወረዳ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
Next article“ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ ከግድቡ ወደ ወደቡ እንሸጋገራለን” የአማኑኤል ወረዳ ነዋሪዎች