“የክልሉን ልማት ለማሳለጥ በፍጥነት፣ በፈጠራ እና በጥራት ተሠርቷል” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

11

 

የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫን በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ተቋማት የሩብ ዓመት አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት የሥራ ዘርፎችን ለይቶ በትኩረት በመሥራቱ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል። የልማት ሥራዎች ላይ የዕይታ ጥልቀት መጨመር እና ጥልቀቱን የተገነዘበ ፕላን ማዘጋጀት በመቻሉ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርጓል ነው ያሉት።

ብዙ ስብራቶች ልማት ላይ ትኩረት እንዳናደርግ ማነቆ ፈጥረው ቆይተዋል ብለዋል። ስብራቶችን ሊያቃና የሚችል ልማትን ለማሳለጥ በፍጥነት፣ በፈጠራ እና በጥራት ለመጓዝ ተሠርቷል ነው ያሉት።

የሕዝብን ተጨባጭ ለውጥ የምናረጋግጥበት፣ ስብራቶችን ሊጠግኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂን መፍጠር የሚቻልበት፣ የሕዝብ የምንጊዜም ጥያቄ የኾኑ የኑሮ ውድነት እና የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱበት፣ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን በአግባቡ የሚያገኙበት ተቋማት በመኾናችሁ በጥልቀት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በሩብ ዓመቱ ሥራን በትጋት ለመፈጸም በትኩረት መሥራት ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ ክፍተቶችን በመለየት የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በከፍተኛ ፍጥነት እና ፈጠራ የምንተገብራቸው ሥራዎች ላይ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና መላመድ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በውይይቱ በክረምት የኮሪደር ልማት መሥራት እንደሚቻል ማሳየት እንደተቻለ እና ፈጣን የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑ ተነስቷል። በሩብ ዓመቱ ተኪ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች መደገፋቸው፣ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በርካታ የአረንጓዴ ፖርኮች መገንባታቸ ተገልጿል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች ቤት የማደስ፣ የመሥራት እና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸው፤ የገበያ ማዕከልን ለማስፋት፤ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን ለማሳደግ ገበያን ለማረጋጋት መሠራቱም ተጠቅሷል።

ቴክኖሎጂን የመጠቀም ሥርዓትን ማስፋት ተችሏል፤ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች በክልሉ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውም ተጠቅሷል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_11_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሕይወቱን ለሀገሩ የሰጠ አሸናፊ ሠራዊት ስላለን ኩራት ይሰማናል” የጊምባ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“ጥራት ያለው ስታትስቲክስ ሳይንሳዊ ፈጠራን ለማሳደግ ወሳኝ ነው” የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ