
ዛሬም የሰላም በሮች አልተቆለፉም፤ የታጠቁ እጆች ይቅርታን እና እርቅን ይዘው ወደ ተዘረጉ የሰላም እጆች እየተቀላቀሉ ነው። “በሰላም፣ በፍቅር እና በወንድማማችነት እንኑር” የሚሉ የተስፋ ድምጽ ጥሪዎችን የሰሙ እና ያስተዋሉ በርካታ አካላት የሰላምን መንገድ ዘላቂ እና አስተማማኝ አማራጭ አድርገው በመምረጣቸው ዛሬ የሰላምን አየር እየተንፈሱ ይገኛሉ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ ባለፉት ሦስት ዓመታት በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት አሰቃቂ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መስተናገዱን ነዋራዎቹ ይናገራሉ። በርካታ ወጣቶች ዓላማ በሌለው ግጭት በመሳተፍ ሕይወታቸውን በከንቱ ገብረዋል፤ ሕዝቡም ቢኾን በደኅንነት ስጋት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ተገድቦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተለይም የታመመ ዘመድ መጠየቅ፤ የሞተን በወጉ መቅበር እና ህሙማንን ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድ የማይቻልበት ደረጃ እንደነበርም አልዘነጉም። ከጎንደር ደባርቅ ባለው መንገድ በተሳፋሪ ላይ የግድያ፣ ዘረፋ እና እገታ ወንጀል ሲፈጸም እንደነበርም አልሸሸጉም።
ይሁን እንጅ ይህን በራስ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስነዋሪ እና አሳፋሪ ድርጊት የተረዱት በርካታ ወጣቶች በየቀኑ የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው እየገቡ ነው ያሉት። ሀገር የምትገነባው በውይይት እንጂ በጥፋት አይደለም የሚሉት ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በርካታ የታጠቁ ኃይሎችን በመምከር እና በመገሰጽ ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
በቀጣይም ቢኾን በወረዳው ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሰፍን ታጣቂዎችን መክሮ እና ዘክሮ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የጀመሩትን በጎ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። አሁን ላይ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን እና የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን ያለምንም የደኅንነት ስጋት እያከናወኑ መኾኑንም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
የወገራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሹመት ዋሴ በወረዳው በተሠሩ የሕዝብ ግንኙነት እና የሰላም ማስፈን ሥራዎች በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲገቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል። በተለይም “ክልሉን ለታሪካዊ ጠላት ኃይሎች አሳልፈን አንሰጥም” በማለት በወረዳው በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው በየቀኑ እየገቡ ነው ብለዋል።
በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ታጣቂዎች በትጥቅ ትግል ሳይኾን በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች እና በአመራሩ ግንዛቤ እየተሠጠ መኾኑንም አቶ ሹመት ጠቁመዋል። በቀጣይ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በማጠናከር የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸው ሌሎችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
