የመኖ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተጀመረው የገፈራ ማምረት ሥራ።

10
በተቀናጀ ዘመናዊ የግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩት ጉልላት መንበረ ከበቆሎ ገፈራ የእንስሳት መኖ የማምረት ሥራን ጀምረዋል። በክረምቱ ወቅት የሚገኙ አረንጓዴ በረከቶችን በመሠብሠብ እርጥበቱን እና አረንጓዴነቱን ጠብቆ ለበጋ ወራት እንዲቆይ ማድረግን ዓላማ አድርገዋል። በገበያ ላይም እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በዘላቂነት እንዲኖር በማድረግ በአርሶ አደሮች እና በአርብቶ አደሮች ዘንድ የሚታየውን የመኖ እጥረት ችግር መቅረፍ መነሻ ኾኗቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በ50 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የለማን በቆሎ በመጠቀም ገፈራ ወደ ማምረት መግባታቸውን ነው የተናገሩት።
ገፈራን (ሳይሌጅ) በወቅቱ እና በጥራት በማዘጋጀት ለወተት እና ለስጋ ከብቶች ከፍተኛ አልሚ ምግብ እና ጤናማ መኖ ማዳረስን ዓላማ አድርገው መነሳታቸውንም ነው የገለጹልን።
በአንድ ሄክታር እስከ 250 ኩንታል እና ከዚያ በላይ ገፈራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ምርቱን ከምጥን መኖ ዋጋ እስከ 40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ለገበያ ለማቅረብ እየሠሩ ነው።
በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን በማስተባበር፣ ልምድ በማካፈል እና አብሮ በማደግ ሰፊ የምርት አውታር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
ትራክተሮችን እና ሌሎች ማሽነሪዎችን በመጠቀም የምርት ሂደቱን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የባንክ ብድር ለማግኘት የመያዣ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ይህም ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈታ እንደሚገባ ነው ያነሱት።
ሥራውን ከነበረበት በብዙ እጥፍ በማሳደግ እስከ 500 ሄክታር መሬት በማልማት የአካባቢውን እና የሀገሪቱን የመኖ ፍላጎት ማሟላት እና ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የቀጣይ ዕቅዳቸው እንደኾነም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የመኖ ልማት ቡድን አሥተባባሪ እና ባለሙያው አበበ ምትኬ አንድ ሄክታር መሬት ከ35 እስከ 40 ቶን የሚደርስ የገፈራ መኖ ማግኘት ያስችላል ብለዋል። ይህም እስከ ስምንት የወተት ላሞችን ለአንድ ዓመት መመገብ የሚያስችል እንደኾነ ገልጸዋል።
ወተት፣ ስጋ እና እንቁላል የሚኾነው መኖ ነው፤ ይሁን እንጂ የአንድ እንስሳት እርባታ ጣቢያ ወጪ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚኾነው ለመኖ የሚወጣ ነው ብለዋል። በመኾኑም አርሶ አደሮች የራሳቸውን ገፈራ መኖ በማዘጋጀት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
በክልል ደረጃ ከ46 በላይ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ይገኛሉ ነው ያሉት። አብዛኛዎቹ የፋብሪካ መኖዎች የተሟላ እና ጥራቱን የጠበቁ ደረጃዎችን ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉም ብለዋል። አሁን ላይ የገፈራ የምርት መጠኑን ከ2 ሺህ ቶን ወደ 4 ሺህ 500 ቶን ለማሳደግ ታቅዶ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የኢትዮጵያ እና የኬንያ ታሪካችን የተሳሰረ እንደመኾኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊኾን ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበደብረ ማርቆስ የማኅበራዊ ተቋማት በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እየተጎበኙ ነው።