“የኢትዮጵያ እና የኬንያ ታሪካችን የተሳሰረ እንደመኾኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊኾን ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

22
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዛሬ በኤልዶሬት ኬንያ በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በኤልዶሬት፣ ኬንያ በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘትና ንግግር በማድረግ ለሀገራቸው ነጻነት ለታገሉ እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ያለኝን ታላቅ ክብር ገልጫለሁ ብለዋል። ለጀግንነታቸው እና ትተውት ላለፉት ዐሻራ የላቀ ክብር አለኝ ነው ያሉት።
የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የዓድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። እነዚህ የጋራ ታሪኮቻችን ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይኾን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መኾኑን ያስገነዝቡናል።
ታሪካችን የተሳሰረ እንደመኾኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊሆን ይገባል። በመደመር መንፈስ፤ኢትዮጵያ እና ኬንያ
ለሕዝቦቻችን ሰፊ እድሎችን እና የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር በንጹሕ ኃይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በንግድ ዘርፎች ያለንን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል።
ዛሬ ክብር ለተቸራቸው ጀግኖች ሁሉ፣ ላቅ ያለ አክብሮቴን አቀርባለሁ። መልካም የማሹጃ (የጀግኖች) ቀን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለተሻለ የትምህርት ዕድገት መምህራን ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleየመኖ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተጀመረው የገፈራ ማምረት ሥራ።