ለተሻለ የትምህርት ዕድገት መምህራን ላይ መሥራት ያስፈልጋል።

8
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በቅድመ ሥራ ሥልጠና መርሐግብር የሚሰጠውን የመካከለኛ ደረጃ የሥራ እና የተግባር ትምህርት የመምህራን ሥልጠናን ለማካሄድ የሚያስችል የጋራ የውይይት እና የስምምነት መድረክ አካሂደዋል።
ስምምነቱ በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች እና በክልሉ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ አለሙ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ሙሉ ስብዕና ያለው፣ ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ባለቤት የኾነ፣ በራሱ የሚተማመን እና ለሀገሩ እና ለወገኑ የሚቆረቆር ዜጋ መገንቢያ ማዕከላት መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ የሥራ እና ተግባር ትምህርት የመምህራን ሥልጠና የትብብር መድረክ የተሻለ፣ ለራሱ፣ ለሀገሩ እና ለወገኑ የሚጠቅም ትውልድ በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ ሀገር የምትቀየርበት የትምህርት ሥርዓት በሁሉም መስክ እያደገ፣ እየተቀየረ እና እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በተለይም ለተሻለ የትምህርት ዕድገት መምህራን ላይ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በትምህርቱ ዘርፍ በተለይም በመምህራን ልማት ዘርፍ ከአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ጋር በጋራ መሥራታችን የተሻለ ዕድል አለው ብለዋል።
ይህ ስምምነት የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅድመ ሥራ ሥልጠና መርሐግብር የሚሰጠውን የመካከለኛ ደረጃ የሥራ እና ተግባር ትምህርት የመምህራን ሥልጠናን በትብብር ለማካሄድ ያስችላል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleትጥቁን በጥበበኛ እጁ ይሠራል፤ ሀገሩን በብርቱ ክንዱ ይጠብቃል!
Next article“የኢትዮጵያ እና የኬንያ ታሪካችን የተሳሰረ እንደመኾኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊኾን ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)