
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ የሙያ እና የዕውቀት ቤትም ነው። ሀገርን በደሙ እየጠበቀ የሀገር ሀብትንም በላቡ ከውድመት ይታደጋል። የመከላከያ ሠራዊቱ በውጊያ ዝግጁነት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትጥቅ፣ በሰው ኀይል ልማት እና መሣሪያን በራስ
አቅም እስከማምረት የደረሰ አቅም እየገነባ ይገኛል። ባለፈው የመንግሥት ሥርዓት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ከአገልግሎት ውጭ ኾነው የቆዩ አያሌ የጦር መሣሪያዎች ዛሬ ላይ በሠራዊቱ የጥበብ እጆች ታድሰው እንደገና ወደ ውጊያ መስመር ተመልሰዋል። የኢፌዴሪ መከላከያ
ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቆዩ በርካታ መሣሪያዎችን መልሶ ወደ ኀይል መቀየር ተችሏል። ወደ ሥራ የተገባውም ዕውቀት፣ አቅም እና የሰው
ኀይል እያለ ኢትዮጵያ ሁሌ ትጥቅ እንድትገዛ ለምን ይደረጋል? በሚል ቁጭት መኾኑን ያብራራሉ። አገልግሎት ሳይሰጡ ተጥለው የነበሩትን መሣሪያዎችን አቧራ አራግፎ በማደስ፣ በመጠገን፣ በማደራጀት እና በመፈተሽ ለሠራዊቱ ማስታጠቅ እንደተቻለ አስረድተዋል። በዚህም ተቋሙ
በገነባው አቅም የተለያዩ አይነት መሣሪያዎችን በአዲስ እንደማምረት የሚቆጠር አስደናቂ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። በተሠራው አስደናቂ ሥራ ከሥራ ውጭ የነበሩ መሣሪያዎችን በራስ አቅም አዘምኖ በመጠቀም የውጊያ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ነው ያሉት። ሥራው የሠራዊቱን
የቴክኒክ እና የመህንድስና ባለሙያዎች አቅማቸውን ያሳዩበት፣ ከፍተኛ ቁርጠኝነት የታየበት፣ አስደናቂ ውጤት የተመዘገበበት ስለመኾኑም አብራርተዋል። ሠራዊቱ በዚህ ዘርፍ አዲስ እና ትልቅ ተሞክሮ ያገኘበት ስለመኾኑም አንስተዋል። ተግባሩ ከውጊያ ባለፈ የሀገር ሀብትን ያዳነ፣
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ያስቀረ የሚያኮራ የሠራዊቱ ውጤት ስለመኾኑም አብራርተዋል። “ይህንን መሣሪያ እንግዛ ብንል ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ነው” ብለዋል። በዚህም የመከላከያ ሠራዊቱ በራሱ የጥበብ እጆች ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
