ፍትሐዊ አገልግሎትን ማስፈን እና ብልሹ አሠራርን መታገል የሁሉም ድርሻ ሊኾን ይገባል።

9
“በመደመር መንግሥት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተፋጠነ ልማት እና ለፍትሐዊ አገልግሎት በጋራ እንቁም” በሚል መሪ መልዕክት ከቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የኅብረተሠብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግሥት የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማጽናት
እየተገበረ ያለውን ሥራ አድንቀዋል። ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎም የከተማዋ የልማት እንቅስቃሴዎች መነቃቃት አሳይተዋል ነው ያሉት። በከተማዋ የሚስተዋለው የንጹሕ
መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮች፣ የተደረጀ ዝርፊያ፣ ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት፣ የመሬት ወረራ፣ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ችግር መፍታት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መፍታት የሚገባቸው ጉዳዮች እንደኾነም አንስተዋል።
የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ ከአዲሱ የመንግሥት ምሥረታ ማግስት የሚካሄደው ይህ መድረክ የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት የሚወሰድበት መኾኑን ተናግረዋል።
የተደራጁ የእገታ እና የዝርፊያ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሠራ ነው ያሉት ከንቲባው ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ ለሕግ ማስከበር ሥራ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አየን ብርሃን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የጸና፤ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተከባብሮ የሚኖር እና ለሕግ የበላይነት መከበር የሚተጋ መኾኑን ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለሚከናወኑ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ስኬታማነት አቅም ኾኗል ነው ያሉት። አካታች አሥተዳደርን ማስፈን፣ ግልጽ እና ፍትሐዊ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ ብልሹ አሠራሮችን ማረም እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራቸው እንደኾኑም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የከተሞችን የመሬት ሀብት በውጤታማነት ለመምራት እና ለአገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleትጥቁን በጥበበኛ እጁ ይሠራል፤ ሀገሩን በብርቱ ክንዱ ይጠብቃል!