
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በዘመናዊ የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ ሥርዓት ግንባታ፣ በካዳስተር ጽንሰ ሃሳብ እና አተገባበር ዙሪያ የዘርፉ የሥራ ኅላፊዎች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ
መሀመድአሚን የሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የከተሞችን ዕድገት ለማፋጠንም ኾነ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናዎን ዘመናዊ የከተማ መሬት አያያዝ ሥርዓት ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኅላፊ ሲሳይ ዳምጤ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት
ለመፍታት እና ለፍትሐዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ የከተማ መሬት አያያዝ ሥርዓት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። የካዳስተር ቴክኖሎጂ ዘመናዊ የከተማ መሬት አሥተዳደር እና የውሳኔ አሰጣጥ አቅምን የሚያጎለብት ነው ያሉት አቶ ሲሳይ የዜጎችን ፍትሐዊ የይዞታ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ
እንደሚያስችልም አመላክተዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ አብዛኞቹ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መነሻ ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መኾናቸውንም ገልጸዋል። “መሬት በሕግ እና በሥርዓት እንዲመራ ዲጂታላይዝድ
የመረጃ አያያዝ ቁልፍ ጉዳይ ነው” ብለዋል። ዶክተር ድረስ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የከተሞችን የመሬት ሀብት በውጤታማነት ለመምራት እና ለአገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ መኾኑንሞ አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
