
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትኩረት ከሚሰጣቸው ሰው ተኮር ተግባራት አንዱ የኾነው የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር ተጀምሯል። በ2015 ዓ.ም በውስን ቁጥር ተጀምሮ የነበረው ይህ መርሐግብር፣ በ2017 የበጀት ዓመት ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ እንደገለጹት፣ በተያዘው የበጀት ዓመት 7 ሺህ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የምገባው ተጠቃሚ ኾነዋል።
መርሐግብሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እና እንዳያረፍዱ ከመታደጉ ባሻገር፣ በትምህርት ውጤታቸው ላይ ተጨባጭ እና ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን መምህራን እና የመምሪያው ኀላፊ ገልጸዋል።
ወላጆች በበኩላቸው መርሐግብሩ ከተጀመረ ወዲህ የምግብ ጭንቀታቸው ቀርቶ የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ መከታተል ላይ ማተኮራቸውን እና በልጆቻቸው ላይም በአካል እና በትምህርት ከፍተኛ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል።
“ከሁሉ በላይ የላቀው ልማት ሰው ላይ የሚሠራው ነው” ያሉት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ፣ የመርሐግብሩን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ እና ባለሀብቶች ከፍተኛ አጋርነት እያሳዩ መኾኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የከተማው ነዋሪዎች የምገባ ድጋፉን ከውኃ ክፍያ ጋር አጣጥመው በመክፈል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከመንግሥት በተጨማሪ የሁሉንም ወገን ተሳትፎ ያቀፈው ይህ የተማሪዎች የምገባ መርሐግብር፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
