ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያዳነ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሠርቷል።

4
“በጎነት ለአብርሆት እና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ሲካሄድ የቆየው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የ2019 ዓ.ም የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ ትውውቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት፤ በክረምቱ መርሐ ግብር ከአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ እስከ ደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመጠገን እስከ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ድረስ በርካታ ሰብዓዊ ተግባራት ተከናውነዋል።
በእነዚህ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ከ84 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን ወጪ ማዳን እንደተቻለ የመምሪያው ኀላፊ ያየሽ ደረሰ ገልጸዋል።
በሂደቱም ከ40 ሺህ በላይ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቁመዋል። በመድረኩ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በረከት ገድፈው በመደጋገፍ እና በመተባበር የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸውን አንስተው፤ መንግሥት ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በግንባር ቀደምትነት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች በተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
መርሐ ግብሩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዕውቅና ሽልማት በመስጠት ተጠናቅቋል።
በቀጣይም በክረምቱ ሲከናወኑ የቆዩ በጎ ተግባራት በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ውጤቶች የሚታዩት ሥንሠራ ብቻ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።