
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንደ ዋነኛ የንግድ እና የዲፕሎማሲ መስመር በመጠቀም ከዓለም ታላላቅ ሥልጣኔዎች መካከል አንዷ እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል። በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የኢትዮጵያ ወደብ የነበረችው አዱሊስ ደግሞ ኢትዮጵያን ከኢሲያ እና ከአውሮፓ ጋር የምታገናኝ የንግድ ማዕከል ነበረች። ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ኾና ቆይታለች፡፡ ይህም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንድታስተናግድ አድርጓታል፡፡
በአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ መምህር እና ተመራማሪ ብነግረው ዋሌ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ብሔራዊ ጥቅምን እና የባሕር በር ጉዳይን አስመልክተው እንደተናገሩት ብሔራዊ ጥቅም ማለት አንድ ሀገር በፖሊሲዎቿ፣ በሕግ ማዕቀፎቿ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶቿ የምታካትታቸው እና የምትተገብራቸው መሠረታዊ ግቦች፣ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች እና ቁልፍ እሴቶች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር አጥታ ለበርካታ ዓመታት የቆየች ናት፣ ለወደብ ኪራይ እና ለመተላለፊያ አገልግሎት ብቻ በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ታወጣለች ብለዋል። ይህ ወጪ ሲሰላ በግለሰብ ደረጃ ከእያንዳንዱ ዜጋ ኪስ በዓመት ቢያንስ ከ35 ሺህ ብር ያላነሰ ወጪ እንዲያወጣ እያደረገ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለወደብ እና ሎጂስቲክስ በየዓመቱ የምታወጣው ወጪ በሦስት ዓመት ውስጥ ብቻ የሚባክነው ገንዘብ አዲስ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ለመገንባት የሚያስችል እንደኾነ ይገመታል ነው ያሉት።
በሌላ አባባል ባለፉት ዓመታት ለወደብ ኪራይ ብቻ የወጣው ጠቅላላ ድምር ከግድቡ ግንባታ ወጪ እጅግ የላቀ ወይም ከሁለት እስከ ሦስት የሕዳሴ ግድቦችን ሊሠራ የሚችል ግዙፍ ገንዘብ መኾኑን መረጃዎች ያመላክታሉ ብለዋል፡፡ የባሕር በር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ብቻ ሳይኾን የሁላችንም የጋራ ጉዳይ በመኾኑ የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት የሚነካ ስለኾነ የጋራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል ነው ያሉት።
ታሪካዊ ዳራ እና መፍትሔዎች፦ ከታሪክ አንጻር ለበርካታ ዘመናት ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር አብረው የኖሩ መኾናቸውን በመገንዘብ ታሪካዊ ዳራውን ይዞ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል። የባሕር በር ባለቤት ለመኾን የሚደረገው ጥረት ሕጋዊ እና ታሪካዊ መሠረት ያለው፣ የሁሉንም ወገን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መኾን አለበት ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
